Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ አየር መንገድም የኢትዮ-እስራኤልን ንግድና ኢንቨስትመንት እያጠናከረ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድም የኢትዮ-እስራኤልን ንግድና ኢንቨስትመንት መጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሚገኝ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ (ዶ/ር) ገለጹ።

አምባሳደሩ ከአዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ÷ኢትዮጵያና እስራኤል ከጥንት መጽሐፍ ቅዱስና ንግስተ ሳባ ዘመናት የሚመነጭ ታሪካዊ ወዳጅነት እንዳላቸው አስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሀገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ዘርፎች ተጠናክሮ መቀጠሉን በማንሳትም÷ በቅርቡ የእስራኤል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የሀገራቱን ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ገልፀዋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) የተመራ ልዑክም ወደ እስራኤል በማቅናት የጋራ ትብብርን የሚያጠናክር ስኬታማ ቆይታ ማድረጉን አንስተዋል።

በንግድና ኢንቨስትመንት መስክም ከ122 ያላነሱ የእስራኤል ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በእርሻ፣ ውሃና ማዕድን ልማት፣ በግብርና ምርት ማቀነባበሪያና በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ እየተሳተፉ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

በንግድም እስራኤል ከኢትዮጵያ ጤፍ፣ ቡና እና ሌሎች የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ከፍተኛ ተቀባይ ሀገር ናት መሆኗን አንስተው ኢትዮጵያም የቴክኖሎጂ ምርቶችን ከእስራኤል እንደምታስገባ እና የሀገራቱ የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ከፍተኛ እድገት እያስዘመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።

ለኢትዮ-እስራኤል ሁለንተናዊ ትብብር በሁለቱ ሀገራት የሚኖሩ ቤተ-እስራኤላውያን ድልድይ ሆነው እያገለገሉ እንደሆነም ነው አምባሳደሩ የገለፁት፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድም በቀን ከሁለት ጊዜ በላይ ወደ እስራኤል የሚያደርገው በረራ የሀገራቱን የቱሪዝም፣ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በማሳለጥ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን እያጠናከረ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.