Fana: At a Speed of Life!

የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታው አዲስ የታሪክ እጥፋት የሚያመጣ ነው – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ግብዓትን በራስ አቅም በመሸፈን ለግብርናው ዘርፍ አዲስ የታሪክ እጥፋት እንደሚያመጣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ኢትዮጵያ ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካ እንደምትገነባ መግለጻቸውን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፥ ይህ ትልቅ ኢኒሼቲቭ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት የሚያፋጥን ነው ብለዋል፡፡

ማዳበሪያን ጨምሮ ግብዓቶችን በራስ አቅም አምርቶ ማቅረብ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ሀገራዊ የምግብ ሉዓላዊነት ግብን ለማሳካት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት የፖሊሲ ርምጃዎች መወሰዳቸውን ጠቅሰው፥የእርሻ ማሽነሪዎች ከቀረጥ ነጻ ወደ ሀገር ገብተው ለአርሶ አደሮች ተደራሽ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ባለፈው የመኸር ወቅት ከታረሰው 20 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት ውስጥ 25 በመቶው በትራክተር መታረሱን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም፥ የምርት ብክነትን በመከላከል ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰጠው ትኩረት የደረሱ ሰብሎችን በኮምባይነር መሰብሰብ እየተለመደ መምጣቱን አንስተዋል፡፡

የሰብል ጤናን ለመጠበቅ የአንበጣ፣ የግሪሳ ወፍና የአረም መቆጣጠሪያ ኬሚካል መርጫ አውሮፕላኖችን በመግዛት ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.