የቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ዘመኑን የዋጀ የፖሊሲ ማዕቀፍ ያስፈልጋል- ሰላማዊት ካሳ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቱሪዝም ሚኒስቴር በቱሪዝም ፓሊሲ ረቂቅ ሰነድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው፡፡
በመድረኩ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ታድመዋል።
ሰላማዊት ካሳ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ በርካታ ታሪካዊ፣ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ የቱሪስት ሃብቶች ያሏት ሀገር ናት።
በዘርፉ በቀዳሚ ተርታ የሚያስቀምጥ እምቅ ሃብት ያላት ሀገር መሆኗንም ነው ሚኒስትሯ ያወሱት፡፡
ከዚህ ቀደም የነበረው ፖሊሲ ረጅም ጊዜ ማስቆጠሩን ጠቁመው÷ ከዘርፉ የሚገኘውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከጊዜው ጋር የሚራመድ የፖሊሲ ማእቀፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ዘርፉን ጊዜውን በዋጀ መልኩ ለመምራት የሚያስችል የፖሊሲ ዝግጅት እና በርካታ አካላት የተሳተፉበት ውይይት በማድረግ ግብዓት ሲሰባሰብ መቆየቱን አስታውሰዋል።
አዲሱ ፖሊሲ ዘርፉ የኢትዮጵያን ገጽታ በጉልህ ለመገንባት እንዲሁም ከዘርፉ የሚገኘውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚያስችል እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።