በኢንስቲትዩቱ ለተመረቱ 11 የፈጠራ ሥራዎች የባለቤትነት ማረጋገጫ ዕውቅና ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን በባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ለተመረቱ 11 የፈጠራ ሥራዎች የባለቤትነት ማረጋገጫ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷በመንግስት ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ የባዮ ኢመርጂንግ ነው።
ለምርምር ልማት ምቹ ሥነ-ምህዳር ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው÷አስፈላጊ የሕግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢንስቲትዩቱ የምርምር ውጤቶችን በማውጣት ተኪ ምርቶችን በማምረት ለሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
የኢትዮጵያ አዕምሮዊ ንብረት ዋና ዳይሬክተር ወልዱ ይመስልበ በኩላቸው÷ዛሬ በአዕምሮ ሃብት ጥበቃ የተመዘገቡት እነዚህ የምርምርና ፈጠራ ውጤቶች እንደ ሀገር ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል።
የምርምር ውጤቶች ችግር ፈቺና የአዕምሮ ጥበቃ መብት ያገኙ ምርምሮችና በተቋሙ ከተሰሩ የምርምር ሥራዎችና ውጤቶች ግንባር ቀደም መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
ኢንስቲትዩቱ በሳይንስ ዘርፍ በቀጣይም ችግር ፈቺና ለሀገር ኢኮኖሚ ጉልህ ፋይዳ ያላቸው ሥራዎች ለመስራት ማቀዱን ተጠቅሷል፡፡
በጀማል አህመድ