በአዲስ አበባ በነዳጅ ማደያዎች የሚታየው ረጃጅም ሰልፍ ምክንያቱ ምንድን ነው?
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፋና ዲጂታል ምሽቱን በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች ባደረገው ቅኝት በአንዳንድ ነዳጅ ማደያዎች ላይ ረጃጅም የተሽከርካሪ ሰልፎች መኖራቸውን ተመልክቷል፡፡
ለአብነትም ሪቼ አካባቢ ባለው የነዳጅ ማደያ ከቴሌ ጋራዥ እስከ ግሎባል ሆቴል ፊት ለፊት ኖክ ማደያ ድረስ፣ ቀይ መስቀል አካባቢ ባለው ነዳጅ ማደያ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር እስከ ጊዮን ሆቴል ፊት ለፊት፣ ከለገሃር የሃ ሕንጻ ጀምሮ እስከ ቅዱስ ዮሴፍ ት/ቤት ፊት ለፊት ረጃጅም የተሽከርካሪ ሰልፎችን መመልከት ተችሏል፡፡
የረጃጅም ተሽከርካሪ ሰልፎች ምክንያትም በናፍታ እጥረት ምክንያት የተከሰተ መሆኑን ፋና ዲጂታል ያነጋገራቸው አሽከርካሪዎች ገልጸዋል፡፡
የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ በቀለች ኩማ በበኩላቸው÷ ባለፉት ቀናት በአንዳንድ አካባቢዎች የነዳጅ እጥረት በተወሰነ መልኩ መከሰቱን ተናግረዋል፡፡
ይህም በጅቡቲ የዒድ አልፈጥር በዓልን ተከትሎ ለሶስት ቀናት ሥራ ባለመኖሩ ነዳጅ ወደ ኢትዮጵያ ካለመግባቱ ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ነው ብለዋል፡፡
የተከሰተውን የናፍታ እጥረት ለመፍታትም ከመጠባበቂያ ዴፖ ለማደያዎች የማከፋፈል ሥራ መሰራቱን ነው ለፋና ዲጂታል ያስረዱት፡፡
የነዳጅ ሰልፉ ከዋጋ ጭማሪ ጋር የማይያያዝ መሆኑን ገልጸው÷በነዳጅ ምርቶች ላይ የዋጋ ማሻሻያ አለመደረጉንም አስገንዝበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ