ወጣት ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አቅም ለውጪው ዓለም እንዲያስተዋውቁ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ወጣት ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያ ቀዳሚ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን ያላትን አቅም የማስተዋወቅ ሥራ እንዲሠሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጠየቀ።
ኮርፖሬሽኑ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ለወጣት ዲፕሎማቶች በኢንቨስትመንትና ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
የኮርፖሬሽኑ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽንና ማርኬቲንግ ዘርፍ ስራ አስፈጻሚ ዘመን ጁነዲን÷ የኢትዮጵያን እምቅ የኢንቨስትመንት አማራጮች ከልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ጋር አያይዘው አብራርተዋል።
በዚህም በመንግስት የተተገበረው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር እና በህንድ ውቅያኖስ አቅራቢያ ያላት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንደሚያደርጋትም ገልጸዋል፡፡
በኢንቨስትመንት እና በዲፕሎማሲ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር፣ የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ውጤታማ ለማድረግና ለሀገሪቱ ዘላቂ ልማት ጥረት እንደሚደረግም መግለፃቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመላክቷል።
ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች፣ ነጻ የንግድ ቀጣና እና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለውን የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳደግ ከባለድርሻዎች ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡