የኢኮኖሚ ትሩፋቶችን ለማሳደግ የብሪክስ አባልነት ፋይዳ የጎላ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 20117 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሪክስ አባል በመሆን የሚገኙ የኢኮኖሚ ትሩፋቶችን ከፍ ለማድረግ አባልነቱ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፈር በድሩ ገለጹ፡፡
“የኢትዮጵያ የኤክስፐርት ተቋማት የብሪክስ ዕይታዎች ለሀገራዊ ህልሞች ስኬት”በሚል መሪ ሐሳብ በጅማ ዩኒቨርሲቲ 2ኛው የብሪክስ ፖሊሲ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጀማል አባፊጣ (ዶ/ር) በውይይቱ ላይ፤ እየተለዋወጠ በሚገኘው የዓለም ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያ ልትከተለው የሚገባትን ስትራቴጂካዊ መንገድ እና የላቀ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብሎም ለማሳደግ የሚጠበቅብንን ኃላፊነት በተግባር እናሳያለን ብለዋል።
ለዚህ ሀገራዊ ትልም መሳካት እንደ ከፍተኛ የትምህርትና የምርምር ተቋም የሚጠበቅብንን ለመወጣት ቁርጠኛ ነን ያሉት ደግሞ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዘውዱ እምሩ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፈር በድሩ በበኩላቸው፤ የኤክስፐርት ተቋማቱ የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁ ለውሳኔ የሚሆኑ ሐሳቦችን ማዋጣት እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰዋል፡፡
የብሪክስ አባል በመሆን የሚገኙ የኢኮኖሚ ትሩፋቶችን ከፍ ለማድረግም አባልነቱ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል፡፡
ሀገራችን በብሪክስ መድረኮች ያላት ተቀባይነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት ወሳኝ በመሆኑ፤ በመድረኩ የሚነሱ ሐሳቦች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ አንፃር ትልቅ ቦታ አላቸው ነው ያሉት፡፡
በተስፋሁን ከበደ