የኩላሊት እና ሽንት ቧንቧ ጠጠር ሕክምና …
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጠጠር ሕመም በዋናነት በኩላሊት፣ ኩላሊትና የሽንት ፊኛን በሚያገናኘው የሽንት ቱቦ እና በሽንት ፊኛ ላይ ይከሰታል።
በዐይን (መሬት ላይ) እንደሚታየው ዓይነት ጠጠር በኩላሊት ውስጥ ሊፈጠር እንደሚችል የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ለጠጠር ሕመም አጋላጭ ከሚባሉ መንስዔዎች መካከል፥ የኩላሊት ሥራ ስኬታማ አለመሆን፣ በቂ ውኃ አለመጠጣት፣ የሽንት መውጫ ቱቦ ክፍት አለመሆን (በተለያየ ምክንያት መዘጋት)፣ ጨው የበዛበት ምግብ እንዲሁም ሥጋ እና እንቁላል አዘውትሮ መጠቀም በዋናነት ይጠቀሳሉ።
ምንም እንኳን እንደጠጠር ዓይነቶቹ ሊወሰን ቢችልም በአብዛኛው፥ ወተትና የወተት ተዋፅዖዎችን ጨምሮ አትክልትና ፍራፍሬ ማዘውተርን ባለሙያዎቹ ይመክራሉ።
የሕመም ምልክቶቹ ጠጠሩ እንደተከሰተበት ቦታ እንደሚለያዩም ያነሳሉ፡፡
ለአብነትም ጠጠሩ ኩላሊት እና የላይኛው ቱቦ ላይ ከተከሰተ፥ በጎን የሰውነት ክፍል (ኩላሊቱ ያለበት ቦታ) ላይ እንዲሁም ከጎን ወረድ ብሎ እስከ ዘር ፍሬ ድረስ ከቀላል እስከ ከባድ የሕመም ስሜት ይኖራል ይላሉ።
አንዳንድ ጊዜ ጠጠሩ ከሽንት ጋር የሚወጣበት ሁኔታ እና ሽንት ደም የሚመስልበት አጋጣሚ እንዳለም ይጠቁማሉ፡፡
በሽንት ፊኛ ላይ የሚከሰት ጠጠር ደግሞ፥ ከእምብርት ወደታች ያዝ ለቀቅ የሚያደርግ የሕመም ስሜት እንዳለው፣ በሚሸኑበት ጊዜም ደም የሚመስል ፈሳሽ ሊታይ እንደሚችል እና ከሽንት ጋር ጠጠር የሚታይበት ሁኔታ መኖሩን ያነሳሉ፡፡
አንዳንድ ጊዜ ምልክት ላይኖረው እንደሚችል የሚገልጹት ባለሙያዎቹ÷ በምርመራ (በአልትራሳውንድ) ግን የሕመሙ መኖር ይታወቃል ይላሉ።
በኩላሊት፣ በሽንት ቱቦ እንዲሁም በሽንት ፊኛ ላይ የሚከሰት የጠጠር ሕመም ዓይነት እንዳላቸው እና አብዛኛዎቹም ከካልሺየም ጋር ሊገናኙ ሆነ ላይገናኙ እንደሚችሉም ነው የሚናገሩት።
ለማንኛውም የጠጠር ሕመም ዓይነቶች የሚሠራ ‘አጠቃላይ ሕክምና’ የሚባል መኖሩንም ይጠቅሳሉ፡፡
የመጀመሪያው በ24 ሠዓታት ውስጥ ከሦስት ሊትር በላይ ውኃ መጠጣት ሲሆን÷ በተለይም ለኩላሊት ጠጠር ተጋላጭ የሆኑ፣ በቤተሰብ ጠጠር ያለባቸው ሰዎች እንዲሁም ጠጠር የነበረባቸውና የዳኑ ውኃ በብዛት መጠጣት አለባቸው ይላሉ፡፡
በእርግጥ ማንኛውም ሰው ለጤናማ ሕይዎት ሲባል ከ2 ነጥብ 5 እስከ 3 ሊትር ውኃ እንዲጠጣ እንደሚበረታታም ያስረዳሉ፡፡
ሌላኛው ሕክምና አመጋገብ ላይ ጨው መቀነስ መሆኑን የሚያነሱት የሕክምና ባለሙያዎቹ፤ ጨው የሚያበዙ ሰዎች ለጠጠር ሕመም የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ሥጋ እና እንቁላልን መቀነስ፤ አትክልትና ፍራፍሬን ማዘውተር ጠጠርን ለመከላከል ብሎም ለማከም እንደሚያግዝ ይገልጻሉ፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት አጠቃላይ ሕክምናዎች ባሻገር፥ ምርመራን መሰረት አድርገው ለእያንዳንዱ የጠጠር ዓይነቶች የሚሰጡ ሕክምናዎች መኖራቸውንም ያብራራሉ፡፡
ጠጠር አንድ ጊዜ ከተፈጠረ ሊደጋገም እንደሚችል፤ ከተደጋገመ ደግሞ ኩላሊትን ሊጎዳ እንደሚችል ይናገራሉ፡፡
ከዚያም ለኢንፌክሽን ሊያጋልጥ ብሎም አንዳንድ ጊዜ ኩላሊትን በቀዶ ጥገና እስከማስወጣት ሊያደርስ እንደሚችል ይናገራሉ፡፡
በመሆኑም የጠጠር ሕመም ከባድ መሆኑን በመገንዘብ ሕብረተሰቡ ለመከላከሉ ትኩረት እንዲሰጥ፤ ከተከሰተም ምርመራ በማድረግ በወቅቱ ሕክምና ሊያደርግ እንደሚገባ የሕክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡
በዮሐንስ ደርበው