Fana: At a Speed of Life!

አፈ-ጉባዔ ታገሰ ዜጎች ለሕገ-መንግሥቱ ተገዢ መሆን እንዳለባቸው አስገነዘቡ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ዜጎች የሕጎች ሁሉ የበላይ ለሆነው ሕገ-መንግሥት ተገዢ ሊሆኑ እንደሚገባ አስገነዘቡ፡፡

“ሕገ-መንግሥትና ሕገ-መንግሥታዊነት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ሦስተኛው የፓርላማ ዜጎች ፎረም ተካሂዷል፡፡

አፈ-ጉባዔ ታገሰ በዚሁ ወቅት በዳረጉት ንግግር፤ ሕገ-መንግሥት የመንግሥትንና የሕዝብን ግንኙነት የአሥተዳደር ሥርዓት የሚደነግግ ሠነድ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ሀገሪቱ የምትመራባቸው ፖሊሲዎችና ሌሎች ሕጎች የሚመነጩት ከሕገ-መንግሥት መሆኑን ጠቁመው፤ ተቋማት የሚገነቡት የሕገ-መንግሥቱን ድንጋጌ መሠረት በማድረግ ነው ብለዋል፡፡

የሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈጻሚው እና የሕግ ተርጓሚው ስልጣንና ተግባር የሥራ ግንኙነት ሕገ-መንግሥቱን መሰረት ያደረገ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 9 ላይ ተቋማትና ዜጎች ሕገ-መንግሥቱን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት እንዳለባቸው የሚደነግግ መሆኑንም አውስተዋል፡፡

ሕገ-መንግሥቱ የሚሻሻልበት ሥርዓት ስለመኖሩም በአንቀጽ 105 ላይ መደንገጉን መግለጻቸውን እና በፎረሙ ላይ ሦስት የመወያያ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት መደረጉን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.