የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ለምርትና ምርታማነት እድገት መረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ፈጣን እና ቀጣይነት ላለው የምርትና ምርታማነት ዕድገት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።
የግብርና ሚኒስቴር ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እና ከክልል ግብርና ቢሮዎች ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ ግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲን ለግብርና አመራሮች፣ ለባለሙያዎች እና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት የማስተዋወቅ መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት÷ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለመጠገን ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል።
ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት በግብርና ስራ ላይ በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ላይ ለዓለም ማሳያ የሆነ ስራ መከናወኑን አንስተዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ኢያሱ ኤልያስ (ፕ/ር) በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ ግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ለግብርና ዘርፍ ባለድርሻ አላካት የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ የምርትና ምርታማነት እድገትን ለማረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሚያዚያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው 31ኛው መደበኛ ስብሰባ ማጽደቁን ይታወሳል።
በማቴዎስ ፈለቀ