ከካርበን ሽያጭ 70 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት የሚያስችል ስምምነት ተደረገ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በካርበን ሽያጭ የ70 ሚሊየን ዶላር የመግባቢያ ስምምነት ከተለያዩ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ማድረጓን የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት፤ በአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ በተከናወነው ዘመቻ በዘርፉ የመጣው ለውጥ ለካርበን ሽያጩ መከናወን አስተዋጽዖ አበርክቷል፡፡
በዚህም ዓለም ባንክን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የ70 ሚሊየን ዶላር የካርበን ሽያጭ የመግባቢያ ስምምነት መደረጉን አስታውቀዋል።
በተለይም የገንዘብ ሚኒስቴር ከኖሮዌይ መንግስት ጋር በፈረንጆቹ 2026 የሚያበቃ ስምምነት ማድረጉን አንስተዋል፡፡
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በደን ልማት ላይ በተሰራው ስራ የሀገሪቱ የደን ሽፋን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማደጉንም አቶ ከበደ ይማም ገልጸዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አራርሳ ረጋሳ÷ ከካርበን ሽያጭ በሚገኘው ገቢ ደን ባለበት አካባቢ የሚገኙ ማህበረሰቦችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
የካርበን ሽያጭን ጥብቅ ደኖች በሚገኙበት አካባቢ ተግባራዊ ለማድረግ የገበያ ማፈላለግ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ተገልጿል።
በጸጋዬ ንጉሥ