የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሀገር ህልውናን በጀግንነቱ ማጽናቱን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተልዕኮውን በአስተማማኝ መወጣቱን እና የሀገር ህልውናንም በጀግንነቱ ማጽናቱን አስታወቀ፡፡፡
የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ በአቪዬሽን ሙያ ተቋሙን ለማገልገል ወደ አየር ኃይል አካዳሚ ለስልጠና የተቀላቀሉ ምልምል የሠራዊት አባላትን በአየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ተቀብለው አነጋግረዋል።
በዚሁ ወቅትም፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የተጣለበትን ተልዕኮ በአስተማማኝ ሁኔታ በመወጣት የሀገር ህልውናንም በጀግንነቱ ያፀና ተቋም መሆኑን ዋና አዛዡ ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ በዚህ ሁሉ የታሪክ ጉዞ ውስጥ ከራሳቸው ይልቅ ሀገር ያስቀደሙና ለኢትዮጵያ ክብር ሲሉ የተዋደቁ ጀግኖችን አፍርቷል ማለታቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ መረጃ አመላክቷል፡፡
ሰልጣኞቹ ተልዕኳቸውን በፅኑ ሊረዱ እንደሚገባ ገልጸው፤ ከወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት እስከ አየር ኃይል አካዳሚ በተዋረድ የሚሰጡትን ስልጠናዎች በብቃት ለማጠናቀቅ ራሳቸውን ብቁ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።