የሌተናል ጄኔራል ጃገማ ኬሎ ጋሻዎችና ጦሮች ለቅርስ ባለስልጣን ተበረከቱ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሌተናል ጄኔራል ጃገማ ኬሎ ሁለት ጋሻዎችና አምስት ጦሮች ለኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ተበረከቱ፡፡
ጋሻዎቹና ጦሮቹ ታላቅ የትግል ዓርበኛ የነበሩት ጃካማ ኬሎ ግለ ታሪካቸው እንዲጻፍና እንዲታተም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት ፒተር ሹልዝ ከ16 ዓመታት በፊት በስጦታ የተበረከቱ እንደነበረ በርክክቡ ወቅት ተገልጿል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረ/ፕ)፤ የታዋቂውና የስመጥሩው ዓርበኛ ሌተናል ጄኔራል ጃካማ ኬሎ ቅርሶችን ለባለስልጣኑ እንዲበረከቱ ላደረጉ አካላት ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
ዓርበኛው ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ቅኝ ግዛትን አልቀበልም በማለት በ15 ዓመታቸው ጠላትን ለመታገል የቆረጡና በበጀግንነት የታገሉ እንደነበሩ አውስተዋል፡፡
በነበራቸው የትግል ጊዜም በወራሪው ኃይል ላይ ከፍተኛ ኪሳራና ጉዳት ያደረሱ በሥራቸውም በርካታ ዓርበኞችን በማሰለፍ ታግለዋል ማለታቸውን የባለስልጣኑ መረጃ አመላክቷል፡፡
ከጦርነትና ከድል በኋላ ጃገማ ኬሎ የሌተናል ጄነራልነት ማዕረግ የተሰጣቸው ሲሆን፤ ፋሺስት ጣሊያንን በመታገልና ሀገራቸውም ነጻነቷን ጠብቃ እንድትቆይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ተብሏል፡፡