Fana: At a Speed of Life!

የህብረቱ ኮሚሽን በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ገለጸ።

የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ከሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ጋር በኪጋሊ ተገናኝተው ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ለአፍሪካ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሩዋንዳ የምታደርገውን አስተዋጽኦ ሊቀመንበሩ አድንቀዋል።

ሩዋንዳ በሰላምና ጸጥታ፣ በመልካም አስተዳደርና በአፍሪካ ህብረት ሪፎርም እንቅስቃሴዎች ላይ የምታደርገውን አስተዋጽኦ እንድታጠናክርም ጠይቀዋል።

በታላላቅ ሐይቆች ቀጣና በተለይም በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰላም ለማስፈን ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ያነሱት ሊቀመንበሩ፤ ኮሚሽኑ ከምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ እና ከደቡብ አፍሪካ ልማት ማህበረሰብ ጋር በመተባበር ለሀገሪቱ ሰላም የድርሻውን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።

መሪዎቹ የህብረቱን የሶማሊያ የድጋፍና ማረጋጋት ተልዕኮን (አውሶም) ጨምሮ በአፍሪካ ለሚመራው የሰላም ዘመቻ ዘላቂ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ተወያይተዋል።

በተጨማሪም አህጉሪቱ ግጭቶችን የመከላከል እና ምላሽ የመስጠት አቅሟን ለማሳደግ እና የአፍሪካን የፀጥታ ችግሮች ለመፍታት የሚመች ሆኖ እንዲቀጥል የአፍሪካን ሰላም እና ደህንነት ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑ መገለጹን የህብረቱ መረጃ አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.