የአፋር ህዝብ በለውጡ ዓመታት አበረታች የልማት ድሎችን ተቀዳጅቷል – አቶ አወል አርባ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፋር ህዝብ በለውጡ ሰባት ዓመታት ፈተናዎችን በፅናት በማለፍ አበረታች የልማት ድሎችን መቀዳጀት መቻሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ።
በሠመራ ከተማ “ትናንት ዛሬና ነገ ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል መሪ ሐሳብ ሀገራዊ ለውጡ እውን የሆነበት ሰባተኛ የማጠቃለያ ውይይት ዛሬ ተካሄዷል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት ፈተናዎችን በፅናት በማለፍ አበረታች የሚባሉ ለውጦች ተመዝግበዋል ብለዋል።
ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ላይ በተምሳሌትነት የሚጠቀሱ የልማት ሥራዎች በሀገር ደረጃ መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
በክልሉም በርካታ የልማት ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀው፤ ይህንን አጠናክሮ ለማስቀጠል ትኩረት እንደሚደረግም ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በብልፅግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን በበኩላቸው በክልሉ ባለፉት ሰባት ዓመታት ገዢ ትርክትን በማስረፅ ረገድ አበረታች ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል።
ፓርቲው አካታችና አሳታፊ ስርዓትን በመተግበር ዜጎች እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ እና ውሳኔ ሰጪነት እንዲጎለብት መስራቱን አብራርተዋል።