ባለ ንስር ዐይኑ ጎል ቀማሚ – ኬ ዲ ቢ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ቁጥሮች አይዋሹም ይባላል፤ በዘጠኝ ዓመት የውሃ ሰማያዊዎቹ ቤት ቆይታው ከሪያን ጊግስ ቀጥሎ በፕሪሚየር ሊጉ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል ስሙን በስኬት መዝገብ አስፍሯል።
ጎል ከማይነጥፍበት የማንቸስተር ሲቲ የፊት መስመር ጀርባ በንስር ዐይኑ አሻግሮ በማማተር ኳስን ሲጠበብባት ዓለም የተመለከተው ኮከብ ከቁጥሮችም በላይ መሆኑን አሳይቷል።
የኳስን መዳረሻ እቅጩን በመመተር ለ174 ጎሎች መቆጠር ቀጥተኛ ሚና የነበረው ቤልጂየማዊው አማካይ፥ 106 ጊዜ ኳስን ከመረብ አገናኝቷል።
የማንቸስተር ሲቲ የጎል ጠንሳሽ ሆኖ ወደ ኢቲሃድ ከመምጣቱ አስቀድሞ ለቼልሲ ተጫውቷል።
በቤልጅየሙ ጁፒለር ፕሮ ሊግ በጄንክ ክለብ በፈረንጆቹ 2009 የተጀመረው የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ህይወቱ በበርካታ ዋንጫዎች ታጅቦ ዘልቋል።
በፕሮ ሊጉ ባሳየው ብቃት በቼልሲ ዐይን ውስጥ መግባት የቻለው ቤልጂየማዊው ኮከብ በ2012 የሰማያዊዎቹ ንብረት በመሆን በቀጣዩ ዓመት በወርደር ብሬመን በውሰት አሳልፏል።
ከአንድ ዓመት የውሰት ቆይታ በኋላ በስታምፎርድ ብሪጅ በቂ ዕድል ማግኘት ሳይችል ሌላኛውን የቡንደስሊጋው ክለብ ዎልቭስበርግን ተቀላቀለ።
በጀርመኑ ክለብ የመጀመሪያ አመት ቆይታው 16 ጎሎችን ከማስቆጠር ባለፈ በአንድ የውድድር አመት 21 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል የቡንደስሊጋውን ሪከርድ የግሉ ማድረግ ችሏል።
በአመቱ ባሳየው ድንቅ ብቃት የቡንደስሊጋው የአመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን ተቀዳጅቷል።
ከዚያም ወደ እንግሊዝ በመመለስ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በዋንጫዎች ያሸበረቁና በግሉም የጎመራባቸውን ስኬታማ አመታት አሳልፏል።
በእነዚህ 10 ዓመታት የኢቲሃድ ቆይታው አንድ የቻምፒየንስ ሊግ፣ ስድስት የፕሪሚየር ሊግ፣ 5 የካራባኦና 2 የኤፍ ኤ ዋንጫዎችን ጨምሮ በድምሩ 19 ዋንጫዎችን መሳም ችሏል።
ኬቨን ዲብሮይን በውድድር አመቱ መጨረሻ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር እንደሚለያይ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ፔፕ ጋርዲዮላ በሰጡት አስተያየት ‘አሳዛኝ ቀን’ ሲሉ ተደምጠዋል።
“እሱ በፕሪሚየር ሊጉ ከተመለከትናቸው ታላላቅ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው፣ በኢቲሃድ መግቢያ ሀውልት እንደሚቆምለት እምነቴ ነው” ሲሉ ፔፕ ስለ ኬቨን ስንብት ሀሳባቸውን ገልጸዋል።
ያለፉት ዓመታት ስኬት ያለ ኬቨን ዲብሮይን የሚታሰብ አይደለም ሲሉም ለነበረው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ዕውቅና ሰጥተዋል።
ኬቨን ዴብሮይን በ2019/20 በአንድ የውድድር አመት 20 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል በቀድሞው የአርሰናል ኮከብ ቲየሪ ሄንሪ የተያዘውን ሪከርድ መጋራቱ ይታወሳል።
የቀድሞው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድንና የመድፈኞቹ አጥቂ ቲየሪ ሄንሪ በአንድ ወቅት ስለ ዲብሮይን በሰጠው አስተያየት፥ ‘ከሌላ ፕላኔት የመጣ ከአዕምሮ በላይ የሆነ ተጫዋች ነው’ ሲል አድናቆቱን ገልጾ ነበር።
በውሃ ሰማያዊው 17 ቁጥር ማሊያ ወርቃማ ጊዜያትን ያሳለፈው ቤልጂየማዊው ድንቅ አማካይ ከማንቼስተር ሲቲ ጋር ሊለያይ መውጫው በር ላይ ተገኝቷል።
ቀጣይ ማረፊያው የት ይሆናል? ዳግም በትልቅ ደረጃ እንመለከተው ይሆን? የእግር ኳሱ ቤተሰብ ጥያቄ ነው።
በኃይለማርያም ተገኝ