በአማራ ክልል የሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የማሰባሰብ ምዕራፍ ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የማሰባሰብ ምዕራፍ ከዛሬ ጀምሮ እንደሚካሄድ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል።
በዚህም አጠቃላይ 4ሺህ 500 የማህበረሰብ ተወካዮች በመጀመሪያዎቹ 4 ቀናት እንደሚወያዩ ተገልጿል።
በቀጣይም የማህበረሰብ ተወካዮች፣ የመንግስት አካላት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የማህበራትና ተቋማት ተወካዮች ይወያያሉ ተብሏል።
በአጠቃላይ በክልሉ ከ6ሺህ በላይ ተሳታፊዎች በአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፉ እንደሚሳተፉ ኮሚሽኑ ገልጿል።
በክልሉ በነበረው የተሳታፊ ልየታ ላይ 19ሺህ 500 የማህበረሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውንም ኮሚሽኑ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።