የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ፍጥነት ከነበረው በመጨመሩ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የባቡር ፍጥነት በሰዓት ከነበረበት 37 ኪሎ ሜትር ወደ 60 ኪሎ ሜትር ማደጉን አስታውቋል፡፡
የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር አክሲዮን ማህበር ለፋና ዲጂታል እንደገለጸው÷የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት በቅርቡ በቀን የነበረውን የምልልስ መጠን ከሁለት ወደ ስምንት አሳድጓል፡፡፡
የባቡሩ የፍጥነት መጠኑም በፊት ከነበረው በሰዓት 37 ኪሎ ሜትር ወደ በሰዓት 60 ኪሎ ሜትር ማደጉን አመልክቷል፡፡
የባቡሩ ፍጥነት መጨመሩን ተከትሎ ሕብረተሰቡ የፍጥነት መሻሻሉን ባለመገንዘብ ለአደጋ እየተጋለጠ መሆኑም ነው የተጠቆመው፡፡
ስለሆነም በኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መስመር አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች የባቡሩ ፍጥነት ከዚህ በፊት ከነበረው መጨመሩን በመገንዝብ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማህበሩ አሳስቧል፡፡
የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር አክሲዮን ማህበር ከዚህ በፊት ጉዳት ሲደርስ ይሰጥ የነበረውን የካሳ ክፍያ ማቆሙንም አስታውቋል፡፡
በመላኩ ገድፍ