Fana: At a Speed of Life!

የአገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርምን ለማስተግበር በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየተሰራ ነው – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ የአገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ለማስተግበር በከፍተኛ ቁርጠኝነት በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

የሪፎርሙ ዓላማ በተመለከተ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ተሳታፊ የሆኑበት የአቅም ግንባታ መድረክ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

“ልህቀት በሰው ተኮር አገልግሎት” በሚል መሪ ሐሳብ በአፍሪካ አመራር አካዳሚ እየተካሄደ በሚገኘው መድረክ ላይ ገንቢ ሐሳቦች እየተገኙበት ነው ሲሉ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

ሪፎርሙ በዋናነት አምስት ዋና ዋና መነሻ ጉዳዮች እንዳሉት ገልጸው፥ ህብረተሰቡን በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ የሚያደርግና አመራሩንና ፈፃሚ አካላትን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድና 2ኛው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራን በስኬት ለመፈፀም የሚያስችል መሆኑን በመጥቀስ፥ በጥልቅ ምክክር እየዳበረና እየበለጸገ የሚሄድ የትግበራ ሂደትን ያነገበ ነው ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር የመንግስትን የመፈፀም አቅም በመገንባት ቀልጣፋ፣ አስተማማኝና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት አሰጣጥን ለመተግበር በር ከፋች እንደሆነም ነው አቶ አደም ፋራህ የገለጹት፡፡

ሂደቱ የመደመርና ፕራግማቲክ አቅጣጫን መሰረት ያደረገ እሳቤን ያገናዘበ፥ ብሎም ስህተቶችን እያረቀ የሚሄድና በሁሉም አካባቢ የሚገኙ ጥንካሬዎችን ደምሮ ለመጠቀም የሚያስችል መርህን የሚከተል መሆኑ የትግበራውን ትሩፋት አጓጊ አድርጎታል ብለዋል።

ሰው ተኮር እሳቤን መሰረት ያደረገና በሲቪል ሰርቪሱ ዙሪያ ያሉ አካላትን በተለይም ተገልጋዩን፣ ሰራተኛውንና አመራሩን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል እንቅስቃሴ ተደርጎ የተቀረጸ መሆኑን አንስተዋል።

አቶ አደም ፋራህ አክለውም፥ ሂደቱ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ፣ ፈጠራና ፍጥነትን ለማሳደግ፣ የተገልጋዩን ጥቅም የሚያስከብር የትግበራ አንጓዎች እንዳሉትም አስረድተዋል።

ሪፎርሙ ከህገ-መንግስቱና ከፌደራል ስርዓቱ ጋር የተጣጣመ ሲሆን የአንድነታችን መገለጫ የሆኑ እሴቶችን ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጡ የሚያደርግ፣ አላስፈላጊ የሆኑ የኢ-ፍትሀዊነት ቅርፊቶችን የሚገፍፍ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በፌደራልና በክልል መንግስታት የጋራ ጥረት ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ ከፍተኛ ተስፋ የተደረገበት ሪፎርም መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ሪፎርሙ ጠንካራና ቅቡልነት ያላቸው ተቋማትን ለመገንባት እድል የሚሰጥ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለትግበራ ሂደቱና ለግቦቹ መሳካት ገንቢ ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.