በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የማንቹሪያን ደርቢ ይጠበቃል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ31ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ማንቼስተር ዩናይትድ በሜዳው ኦልድትራፎርድ የከተማ ተቀናቃኙን ማንቼስተር ሲቲን ምሽት 12 ሰዓት ከ 30 ላይ ያስተናግዳል።
በውድድር ዓመቱ ወጥ ብቃት ማሳየት የተሳነው እና በ37 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቼስተር ዩናይትድ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።
በ51 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ተጋጣሚው ማንቼስተር ሲቲ ተከታታይ ሶስተኛ ጨዋታውን በሊጉ ለማሸነፍና በሚቀጥለው የውድድር ዓመት የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ ለመሆን በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ለመቆየት ይፋለማል።
ሁለቱ ቡድኖች በሁሉም ውድድር ባደረጓቸው ያለፉት አምስት የእርስበርስ ጨዋታዎች ማንቼስተር ሲቲ በሶስቱ ሲያሸንፍ ማንቼስተር ዩናይትድ ደግሞ በሁለቱ ድል ቀንቶታል።
በዚህ የውድድር ዘመን ሁለቱ ቡድኖች በኢትሀድ ስታዲየም ባደረጉት የመጀመሪያ ዙር የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ማንቼስተር ዩናይትድ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል።
በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ከማንቼስተር ሲቲ ጋር የሚለያየው ቤልጂየማዊው የመሀል ሜዳ ኮከብ ኬቨን ዲብሮይን የመጨረሻ የማንቹሪያን ደርቢ ጨዋታውን ያከናውናል ።
ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞ ቀን 10 ሠዓት ላይ የሊጉ መሪ ሊቨርፑል ወደ ክራቨን ኮቴጅ አቅንቶ ፉልሀምን ይገጥማል።
73 ነጥብ በመሰብሰብ ሊጉን እየመራ የሚገኘው ሊቨርፑል ጨዋታውን የሚያሸንፍ ከሆነ ከተከታዩ አርሰናል ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ 14 ከፍ ያደርጋል።
በ45 ነጥብ 10 ደረጃ ላይ የተቀመጠው በማርኮ ሲልቫ የሚመራው ፉልሀም፤ ከጨዋታው ሶስት ነጥብ ማሳካት ከቻለ ነጥቡን ወደ 48 ከፍ በማድረግ 8ኛ ደረጃ ላይ ይቀመጣል።
ሁለቱ ቡድኖች በሁሉም ውድድር ካደረጓቸው ያለፉት አምስት የእርስበርስ ግንኙነቶች ሊቨርፑል በሶስቱ ሲያሽንፍ በቀሪው ሁለት ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።
በተመሳሳይ ቀን 10 ሠዓት ላይ ብሬንትፎርድ ከቼልሲ እንዲሁም ቶተንሀም ሆትስፐር ከሳውዝሃምፕተን ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በወንድማገኝ ፀጋዬ