የነቀምቴ -አንገር ጉቲን-አንዶዴ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታን ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የነቀምቴ – አንገር ጉቲን-አንዶዴ የአስፋልት ኮንክሪት የመንገድ ግንባታን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታውቋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን የሚገኘው ፕሮጀክቱ 86 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ሲሆን÷ ከነቀምቴ ከተማ እስከ አንዶዴ የሚዘልቅ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
አሁን ላይም የአስፋልት ንጣፉ (21 ኪ.ሜ፣ የአፈር ቆረጣ እና ሙሌት (25 ነጥብ 23 ኪ.ሜ)፣ የድሬኔጅ ሥራዎች( 69 በመቶ)፣ ሰብ ቤዝ ንጣፍ (22 ኪ.ሜ)፣ ቤዝ ኮርስ ንጣፍ ( 21 ኪ.ሜ) እንዲሁም በርካታ የስትራክቸው ሥራዎች መከናወናቸው ተጠቅሷል፡፡
ለግንባታ ማስፈጸሚያ1 ቢሊየን 948 ሚሊየን 446 ሺህ ብር በላይ በጀት የተያዘ ሲሆን ÷ወጪው በዓለም ባንክ የሚሸፈን መሆኑን የአስተዳደሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
የመንገድ ግንባታው መጠናቀቅ ከዚህ በፊት የነበረውን የትራንስፖርት ችግር በመቅረፍ ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ወደ ፈለጉበት ቦታ የሚንቀሳቀሱበትን ሁኔታ እንደሚፈጥር ተገልጿል፡፡
አርሶ አደሮች ምርታቸውን ወደ ማዕከላዊ እና የውጪ ገበያ በቀለሉ እንዲያቀርቡ ከማድረጉ ባለፈ የአምራቾችንና ሸማቾችን ትስስር ለመፍጠር ሚናው ጉልህ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
መንገዱ በዞን እና በወረዳ 21 ነጥብ 5 ሜትር፣ በቀበሌ 12 ሜትር እና በገጠር 7 ሜትር የጎን ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ ነው እየተገነባ ነው የሚገኘው ።