እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር እንደምታጠናክር ገለጸች
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ከእስራኤል ም/ቤት አፈ ጉባዔ አሚን ኦሃና ጋር ተወያይተዋል፡፡
ውይይቱ በኡዝቤኪስታን እየተካሄደ ከሚገኘው 150ኛው የኢንተር ፓርላሜንታሪ ኅብረት መድረክ ጎን ለጎን ነው የተደረገው፡፡
በውይይታቸውም ኢትዮጵያ እና እስራኤል ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
አፈ ጉባዔ አገኘሁ÷ ኢትዮጵያና እስራኤል ዘመናትን የተሻገረ መልካም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና በዘመናዊ ግብርና ዘርፎች ያለውን ትብብር አጠናክሮ መቀጠል እንደሚፈልግም አንስተዋል፡፡
በተጠቀሱት ዘርፎች ዙሪያ በትብብር መሥራት ሁለቱን ሀገራት ይበልጥ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
የእስራኤል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አሚን ኦሃና በበኩላቸው÷ እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
ሀገራቱ አሁን ያላቸው አኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲያድግ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡