የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተደረጉ ማሻሻያዎች ውጤት እያመጡ ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተደረጉ ማሻሻያዎች ውጤት እያመጡ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት በምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ ከተማ 1 ሺህ 402 የእርሻ ትራክተሮችን ለአርሶ አደሮች እና ለማህበራት አስረክቧል።
ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በክልሉ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤታማ የማሻሻያ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።
ከዚህ በፊት ለአርሶ አደሩ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማነቆ የነበሩ አሰራሮችን በማሻሻል በግብርና ዘርፍ እድገት እየተመዘገበ መሆኑን አመልክተዋል።
ለአብነት ከዚህ በፊት ትራክተሮችና ሌሎች የግብርና መሳሪያዎች ከውጭ ሲገቡ ከፍተኛ ቀረጥ ይጣልባቸው እንደነበር ጠቅሰው÷አሁን ላይ የግብርና መሳሪያዎችን ከታክስ ነፃ በሆነ መንገድ በማስገባት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
የክልሉ አርሶ አደር የእርሻ መሳሪያዎችን በብድር እንዲያገኝ እድል መመቻቸቱን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለጹት፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ በሪሶ ፈይሳ በበኩላቸው÷ በክልሉ በትኩረት እየተተገበሩ ካሉ ተግባራት መካከል የግብርና ሜካናይዜሽን አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በተሰሩ ሥራዎች በምርትና ምርታማነት እድገት ላይ ለውጥ መምጣቱን ጠቅሰዋል÷በአሁን ወቅት በክልሉ 8 ሺህ ትራክተሮች እንዳሉ ጠቁመዋል።