በቀጣናዊና ባለብዙ ወገን ትስስር የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር እየተሰራ ነው – ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቀጣናዊ እና ባለብዙ ወገን ትስስር የኢትዮጵያን ጥቅም በዘላቂነት ለማስከበር በትኩረት እየተሰራ ነው ሲሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ
የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የንግድና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አሻ ያህያ እና ሌሎች የኮሚቴው አባላት በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የመስክ ምልከታ አድርገዋል፡፡
ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ለቋሚ ኮሚቴው ሚኒስቴሩ ባለፉት 9 ወራት የነበረውን የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ ማብራሪያ መስጠታቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
በማብራሪያቸውም በንግዱ ዘርፍ በተከናወኑ የአሰራር ማሻሻያዎች ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ ትርጉም ያላቸውን ውጤቶች መገኘታቸውን አንስተዋል፡፡
ለአብነትም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከወጪ ንግድ 4 ነጥበ 5 ቢሊየን ዶላር መገኘቱን ነው ያስረዱት፡፡
በዓመቱ መጨረሻ ከ5 ቢሊየን ዶላር በላይ ለማስገባት እየተሰራ ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷በጥራት ልሕቀት፣ በቀጣናዊና ባለብዙ ወገን ትስስር የኢትዮጵያን ጥቅም በዘላቂነት ለማስከበር በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
ከቋሚ ኮሚቴው የሚሰጡ ጠንካራ ጎኖችን እንደ ግብዓት በመውሰድና የታዩ ክፍተቶችን በማረም በበጀት ዓመቱ መጨረሻ አመርቂ አፈጻጸም ለማስመዝገብ እንደሚሰራም አመላክተዋል፡፡