Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝነትን የሚያቀላጥፉ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ወደ ተግባር ገብተዋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝነትን የሚያቀላጥፉ ፖሊሲዎች እና መመሪያዎች ፀድቀው ወደ ተግባር መግባታቸው ተገለጸ።

የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) የዩኒቨርሲቲውን ሪፎርም ሂደትና የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል አከባበርን አስመልክቶ እንዳሉት፤ ራስ ገዝነት የአካዳሚ እና የአስተዳደር ነፃነትን ያረጋግጣል።

በተጨማሪም ለሀብት ምንጭነት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እና ጥራት ያለው የትምህርትና የሥራ ከባቢ መፍጠርም የራስ ገዝነት ዓላማዎች መሆናቸውን አንስተዋል።

የዩኒቨርሲቲው የራስ ገዝ ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቶ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ፀድቆ ወደ ሥራ ገብቷል ነው ያሉት።

በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው በ75 ዓመታት ጉዞው ለሀገር ብዙ ወረት ያከማቸና ትልቅ ስብእና የገነቡ ሰዎችን የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የአልማዝ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓሉን አስመልክቶ የምርምር ኮንፈረንሶች፣ ስፖርታዊ ውድድሮች፣ እውቅና አሰጣጥ እና አውደ ርዕይም እንደሚኖር ጠቁመዋል።

በየሻምበል ምህረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.