የቻይና “ቤልት ኤንድ ሮድ” ፕሮጀክት የኢትዮጵያን ልማት የሚደግፍ ነው – አምባሳደር ተፈራ ደርበው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ቻይና እየተገበረች ያለው “ቤልት ኤንድ ሮድ” ኢኒሼቲቭ የኢትዮጵያን የልማት እቅድ የሚደግፍ መሆኑን በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ገለጹ።
አምባሳደር ተፈራ የቻይና “ቤልት ኤንድ ሮድ” አኒሼቲቭ ዋነኛ አካል የሆነውና በኤሌክትሪክ የሚሠራው የአዲስ አበባ-ጂቡቲ የምድር ባቡር ግንባታ ከኢትዮጵያ የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ ጋር የተሰናሰለ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
55 ዓመታትን የተሻገረው የኢትዮ-ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጥብቅና ጥልቅ መሆኑን ያነሱት አምባሳደር ተፈራ÷ ተፈጥሯዊና ከፍተኛ ጥራት ያለው የኢትዮጵያ ቡና በቻይና ተጠቃሚዎች ዘንድ ከፍተኛ ተፈላጊነት እንዳለው አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ቻይና የምትልከው የቡና ምርትም ባለፉት ሦስት ዓመታት 27 በመቶ ዓመታዊ እድገት ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
የሁለቱ ሀገራት የንግድ ግንኙነት በየዓመቱ 17 ነጥብ 5 በመቶ እያደገ በፈረንጆቹ 2024 የ3 ነጥብ 55 ቢሊየን ዶላር ግብይት እንደተደረገ የቻይና ጉምሩክ አስተዳደር መግለጹን ቻይና ዴይሊ ዘግቧል።
ቻይና የኢትዮጵያ ታላቋ የንግድ አጋርና የኢንቨስትመንት ምንጭ መሆኗን የገለጹት አምባሳደር ተፈራ÷ ይህም ከአስር ዓመታት በፊት ጀምሮ ተግባራዊ በተደረገው የ“ቤልት ኤንድ ሮድ” ኢኒሼቲቭ መሆኑ አመላክተዋል።
ይህም ቡና እና ሌሎች ምርቶችን ጨምሮ ወደ ውጭ የምንልካቸውን የግብርና ምርቶች እንዲጨምር ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል።