የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአማራ ክልል የማህበረሰብ ወኪሎች ምርጫ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከመጋቢት 27 ጀምሮ በአማራ ክልል ከ10 የህብረተሰብ ተወካዮች አጀንዳ እያሰባሰበ ይገኛል።
ሰሞኑን በአጀንዳዎቻቸው ላይ ሲመክሩ የነበሩት 4 ሺ ህ 500 የህብረተሰብ ወኪሎች አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ዛሬም የቀጠለ ሲሆን፤ ወኪሎቹ በጠቅላላ ሀገራዊ ጉባኤው እና በክልል የባለድርሻ አካላት መድረክ የሚወክሏቸውን እየመረጡ ይገኛሉ።
በክልሉ በአጠቃላይ 270 የሚደርሱ የወረዳ ማህበረሰብ ወኪሎች ይመረጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ወኪሎቹ ሰሞኑን ምክክር ሲደረግባቸው የነበሩ አጀንዳዎችን እንደሚያጠናቅሩና በባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ላይ እንደሚሳተፉ ተነግሯል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የመንግስት አካላት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እና ማህበራትን ጨምሮ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም በባህርዳር እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።
በመሳፍንት እያዩ