Fana: At a Speed of Life!

የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች አንድነቷ የተጠናከረ ሀገር በመገንባት ረገድ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ኅብረ-ብሔራዊ አንድነቷ የተጠናከረ ሀገር በመገንባት ረገድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ይህን እንዲያጠናክሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) አሳሰቡ፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት “ዓላማ ተኮር ተግባቦት ለኢትዮጵያ መንሠራራት” በሚል መሪ ሐሳብ ለከተማ እና ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መዋቅር አመራሮች እና ከፍተኛ ባለሙያዎች የዐቅም ግንባታ ሥልጠና እየሰጠ ነው።

በስልጠናው ላይ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) “ገዥ ትርክት ግንባታ እና የኮሙኒኬተሮች ሚና” በሚል ርዕስ ጽሑፍ ማቅረባቸውን የአገልግሎቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

በዚሁ ወቅትም፤ የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች በሕዝቦች መካከል ትሥሥር በመፍጠርና የአብሮነት ዕሴቶችን በማሳደግ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነቷ የተጠናከረ ሀገር በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው አስገንዝበዋል፡፡

በዓላማ ተኮር ተግባቦት ላይ ተመሥርቶ የኢትዮጵያን መንሠራራት ማብሠር የኮሙኒኬሽን መዋቅሩ ትኩረት ሊሆን እንደሚገባ ያስገነዘቡት ደግሞ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ከበደ ዴሲሳ ናቸው፡፡

የኮሙኒኬሽን መዋቅሩ ሁሉንም የሚዲያና ኮሙኒኬሽን አማራጮች ተጠቅሞ ብሔራዊ ትርክትን በመገንባት፤ የመንግሥትን ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች እና መነሣሣቶች የማስተዋወቅ ብሎም የማስረጽ ሚናውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

ብሔራዊ ጥቅሞችን ተገንዝቦ፣ በተለዋዋጭ ዓለም አቀፋዊ፣ አኅጉራዊ እና ቀጣናዊ ሁኔታዎች ውስጥ ዐውዱን የሚመጥን የመረጃ ተደራሽነት ሥርዓት በመፍጠር፣ ሐሰተኛ መረጃዎችን እና የጥላቻ ንግግሮችን የሚሞግት የኮሙኒኬሽን ሥርዓት እውን ለማድረግ ሥልጠናው አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.