ኢትዮጵያ እና ቱርክሜኒስታን ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) እና የቱርክሜኒስታን አቻቸው ረሺድ ምሬዶቭ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል፡፡
ሚኒስትሮቹ በስልክ ባደረጉት በውይይት÷ የሁለቱን ሀገራት ትብብር በኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ለማሳደግ ብሎም የሀገራቱን የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ውይይት ማጎልበት፣ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር መተባበርን እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ከመፍጠር አንጻር በጋራ ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት ዘርፈ ብዙ እና ዘላቂ ግንኙነትን ለመገንባት ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸው÷ የሀገራቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጉብኝት እንዲደረግ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ተስማምተዋል፡፡
ሚኒስትሮቹ ኢትዮጵያ እና ቱርክሜኒስታን በኢኮኖሚው ዘርፍ፣ በቀጣናዊ መረጋጋት እና ትብብር ላይ በጋራ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡