Fana: At a Speed of Life!

የትግራይ ህዝብ ሰላምና መረጋጋት አግኝቶ በልማት ተጠቃሚ እንዲሆን የፌደራል መንግስት ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ህዝብ ሰላምና መረጋጋት አግኝቶ በልማት ተጠቃሚ እንዲሆን የፌዴራል መንግስት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የርዕሰ መስተዳድርነት ርክክብ ሥነ-ሥርዓት በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የትግራይ ህዝብ ሰላምና መረጋጋት አግኝቶ በልማት ተጠቃሚ እንዲሆን የፌዴራል መንግስት ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ አቶ ጌታቸው ረዳ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ጀምሮ ላለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ ሰላም የማስፈን ፍላጎትን እውን ለማድረግ ለሰጡት የማይናወጥ የጸና ቁርጠኛ አመራር ምስጋና አቅርበዋል።

የትግራይን ህዝብ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሰላም እንዲያገኝ የፈጸሙት ታላቅ ተግባር በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነም ገልጸዋል።

ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ በቀጣይ የጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድርነት ኃላፊነታቸው፥ የአቶ ጌታቸው ረዳን ፈለግ በመከተል ሰላምን እንደሚያጸኑ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ለአንድ ወር ያህል ጊዜ የኢትዮጵያን ሕገ-መንግስት፣ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነትና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡን ምክር በማከል ሰፊ ውይይት ሲካሄድ መቆየቱን አስታውሰዋል።

የአቶ ጌታቸው የስልጣን ዘመን በሕጉ መሰረት ሲያበቃ ቀሪ ቁልፍ ስራዎች የሚያከናውን አካል እንደሚያስፈልግ ድምዳሜ ላይ መደረሱን ጠቁመው፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩን መርቶ ከግብ የሚያደርስ አካል ለመሰየም ሰፊ ውይይት ሲደረግ መቆየቱን አብራርተዋል።

በተካሄደ ውይይት ማሟላት የሚገባቸው የሕግ ክፍተቶች እንዳሉ ግንዛቤ መወሰዱን ጠቁመው፤ በዚህም በአዋጅና በአሰራር ሊታረሙ የሚገባቸውን ጉዳዮች በማስተካከል በሰላማዊና አዲስ ባህል የስልጣን ሽግግርና ቅብብሎሽ መደረጉን ተናግረዋል።

የአዋጅ ማሻሻያ በማድረግ አሰራርን የተከተለ ስኬታማ የርክክብ ሥነ-ስርዓት መካሄዱንም አስረድተዋል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ርዕሰ መስተዳድር የክልሉ ህዝብ የጠማውን ሰላም፣ ልማት እና እንደሌሎች ወንድሞቹ ወጥቶ የመግባት መሻት በማሳካት ለኢትዮጵያና አፍሪካ ጠቃሚ የሆነ ስራ በመስራት ታሪክ የሰጣቸውን ዕድል እንዲጠቀሙበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የፌደራል መንግስት የትግራይ ህዝብ ሰላም አግኝቶ እንደሌሎች ወንድሞቹ በኢትዮጵያ እየመጣ ያለውን ለውጥ እንዲቋደስ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚደረግ ማረጋገጣቸውን የኢዜአ መረጃ አመላክቷል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ለተሰየሙት ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደም ቀጣይ ስራቸው ቀናዒ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድርነትን ተረክበው የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር የተልዕኮ አፈጻጸም የቃል ኪዳን ሰነድን ፈርመዋል።

በሥነ-ስርዓቱም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.