የትግራይ ክልል ግዜያዊ ርዕሰ መስተዳድር ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ለእውነተኛ ሰላም ገንቢ ሚና ይጫወታል- ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ክልል ግዜያዊ ርዕሰ መስተዳድር ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ለእውነተኛ ሰላም ገንቢ ሚና እንደሚኖረው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት (ኢጋድ) ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ወርቅነህ ገበየው (ዶ/ር) በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ÷ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግሩ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት የሚያጸና ስለመሆኑ አስታውቀዋል፡፡
የዛሬው አይነት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የህዝብ ፍላጎትን ያስቀደመ መሆኑን ኢጋድ ያምናል ሲሉም አመላክተዋል፡፡
ይህም ለዘላቂ ሰላም ሚና እንዳለው ገልጸው÷ ሽግግሩ እንዲሳካ በሳል አመራር ለሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ዋና ጸሐፊው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ለተመረጡት ሌ/ጄኔራል ታደሰ ወረደም የእንኳን ደስ ያልዎት መልዕክት በማስተላለፍ መልካም የስራ ጊዜን ተመኝተዋል፡፡
በጊዜያዊ አስተዳደርነት ባለፉት ሁለት ዓመታት ሚናቸውን የተጫወቱት አቶ ጌታቸው ረዳም የሰላም ስምምነቱ እውን እንዲሆን ላደረጉት አበርክቶ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡