Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና አውሮፓ ህብረት ያላቸውን ግንኙነት በኢኮኖሚው ዘርፍ ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ እና አውሮፓ ህብረት መካካል ያለውን መልካም ግንኙነት በኢኮኖሚው ዘርፍ ለማጠናከር ያለመ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በሲሞን ሞርዲ ከተመራ የአውሮፓ ህብረት ልዑካን ቡድን ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

ውይይቱ የግሉ ዘርፍ ለኢኮኖሚ እድገት ያለውን ፋይዳ በተመለከተ እንዲሁም ሁለቱ ወገኖች በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፎች በጋራ በሚሰሩበት አግባብ ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያ እና አውሮፓ ህብረት ግንኙነታቸውን የጀመሩበት 50ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በተደረገው ውይይት ሁለቱ ወገኖች ትብብራቸውን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን አመላክተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ በውይይታቸው ወቅት ባደረጉት ገለጻ÷ ኢትዮጵያ ያካሄደችው የኢኮኖሚ ሪፎረም የግሉን ዘርፍ ለማበረታት ያለመ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በዚህም ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ አይነኬ የነበሩ ተቋማት የግሉን ዘርፍ ማሳተፍ መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት ልዑክ መሪ ሲሞን ሞርዲ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት የነበራቸው ሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ንግድ፣ ዘላቂ የስራ ፈጠራ እና ኢንቨስትመንት ትብብር ማደጉ ጠቃሚ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

ሁለቱ ወገኖች ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆናቸውን በውይይቱ ወቅት መግለፃቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.