በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ባርሴሎና ከቦርሲያ ዶርትሙንድ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ቀጥለው ሲደረጉ ባርሴሎና ከቦርሲያ ዶርትሙንድ እንዲሁም ፒኤስጂ ከአስቶንቪላ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የካታላኑ ክለብ ባርሴሎና ምሽት 4 ሠዓት ላይ በሜዳው የጀርመኑን ክለብ ቦርሲያ ዶርትሙንድን ያስተናግዳል።
በሀንሲ ፍሊክ የሚመራው ባርሴሎና በጥሎ ማለፉ ጨዋታ ቤኔፊካን፤ ዶርትሙንድ ደግሞ ሊልን በማሸነፍ ለሩብ ፍፃሜው መድረሳቸው ይታወሳል።
በተመሳሳይ ምሽት 4 ሠዓት ላይ ፒኤስጂ በሜዳው ፓርክ ደ ፕሪንስ የእንግሊዙን ክለብ አስቶንቪላን ያስተናግዳል።
በጥሎ ማለፍ ጨዋታ የፈንሳዩ ክለብ ፒኤስጂ ሊቨርፑልን እንዲሁም አስቶንቪላ ክለብ ብሩዥን በመርታት ወደ ሩብ ፍፃሜው መግባታቸው ይታወቃል።
የፈረንሳይ ሊግ ኧ ዋንጫን ማሳካቱን አስቀድሞ ያረጋገጠው ፒኤስጂ፤ በተጨማሪ ዋንጫ ፉክክር ውስጥ ለመቆየት ይፋለማል።
የእንግሊዙ አስቶንቪላ በሁሉም ውድድር ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ምንም ሽንፈት አላስተናገደም።
ባለሜዳው ቡድን ፒኤስጂ በሁሉም ውድድር ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ድል አድርጓል።
በወንድማገኝ ፀጋዬ