የኔዘርላንድስ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) የኔዘርላንድስ ኩባንያዎች የኢኮኖሚ ማሻሻያው የፈጠረውን ምቹ ዕድል በመጠቀም የኢንቨስትመንት ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቀረቡ፡፡
ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ከኔዘርላንድስ አምባሳደር ክርስቲን ፒሬን ጋር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ወቅታዊ ሁኔታና በቀጣናዊ የሰላምና ደኅንነት ላይ ሚኒስትሩ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በተጨማሪም መንግሥት ያካሄደው ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል መፍጠሩን ማስረዳታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
ይህን ዕድል ለመጠቀምም የኔዘርላንድስ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያላቸውን ኢንቨስትመንት ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡