በዕውቀት ብቁ የሆኑ አመራሮችና ባለሙያዎችን ለማፍራት አበረታች ሥራ እየተሠራ ነው- ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በዕውቀትና ክኅሎት ብቁ አመራሮችና ባለሙያዎችን ለማፍራት አበረታች ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
በብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ለፓርቲው የኮሙኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት አመራሮች እና ባለሙያዎች “የድኅረ እውነት ዘመንን በእውቀት እና በእውነት” በሚል መሪ ሐሳብ ስልጠና በአዲስ አበባ ተጀምሯል።
ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በስልጠናው ማስጀመሪያ እንዳሉት፤ የሀገራችንን የለውጥ ጉዞ ለማጠናከር እና የሕዝባችንን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ዘመኑን የዋጀ ዕውቀትና ክኅሎት በመያዝ ሐሰተኛ መረጃዎችን መመከትና እውነተኛ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ ይገባል።
በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው፤ ዘመኑ መረጃዎች በቴክኖሎጂ ተቀምመው እውነቱንና ሐሰቱን ለመለየት አስቸጋሪ በሚሆን አግባብ የሚሰራጩበት የድኅረ-እውነት ጊዜ በመሆኑ ይህን የሚመጥን ዝግጁነት መላበስ ይገባል ብለዋል፡፡
ፓርቲው በመደመር እሳቤ የሀገራችንን ትርክት በቅጡ ተረድቶ የብሔራዊነት አሰባሳቢ ትርክት ለመገንባት እየተረባረበ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ይህንን ሐቅ በዕውቀት እና በክኅሎት ማሳወቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡