በክልሉ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በተቀረጹ ኢኒሼቲቮች ውጤት እየተመዘገበ ነው – አቶ አሻድሊ ሀሰን
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በተቀረጹ ኢኒሼቲቮች አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገልጸዋል።
በአሶሳ ከተማ እየተካሄደ ባለው 9ኛ ዙር ክልላዊ የግብርና ዘርፍ የባለድርሻ አካላት መድረክ ላይ ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ክልሉ ለግብርና ልማት ተስማሚ ስነ-ምህዳር ያለው በመሆኑ ምርታማነትን በማሳደግ የተጀመረውን ሁለተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል።
የአርሶ አደሩን የቴክኖሎጂና የግብዓቶች አጠቃቀም ለማሻሻል በተደረገ ጥረት ውጤት መመዝገቡን ገልጸው፤ ለአፈር ለምነት አስተዋጽኦ ያላቸውን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ግብዓቶች በመጠቀም ምርታማነት እየጨመረ መምጣቱንም ጠቁመዋል።
በሌማት ትሩፋት፣ በአረጓዴ አሻራ፣ በስንዴና በሩዝ ምርት ልማት ዘርፍ የተገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ማስገንዘባቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።