ዴንማርክ በመጠጥ ውኃ አቅርቦት ዘርፍ የምታደርገውን ድጋፍ እንደምታጠናክር ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሰደር ከሆኑት ሱን ክሮግስትሩፕ ጋር በትብብር በሚሠሩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም፤ የዴንማርክ መንግሥት በዐቅም ግንባታ፣ በቴክንካዊ ድጋፍ እና በታዳሽ ኃይል ልማት ኢንቨስትመንት ላይ በተለይም በንፋስ ኃይል ልማት በትብብር እየሠራ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በቆላማ እና ውኃ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ላይ በሚተገበረው ፕሮግራም ላይም እንዲሳተፉ መጠየቃቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
አምባሰደር ሱን ክሮግስትሩፕ የዴንማርክ መንግሥት በተለያዩ ዘርፎች በትብብር እየሠራ መሆኑን አንስተው፤ የአሰላ የነፋስ ኃይል ማመንጫ በታዳሽ ኃይል ልማት ላይ የሚደረገው ትብብር ማሳያ ነው ብለዋል።
የዋሽ ፕሮግራምን በተለየ አቀራረብ ለመደገፍም ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡