ከብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ
ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ሚያዝያ 1 ቀን 2017 ባደረገው ስብሰባ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለማዊ ሁኔታዎችን ገምግሟል፡፡
ኢትዮጵያ ለዘመናት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ስብራቶች ገጥመዋት ነበር፡፡ እነዚህን ስብራቶች በመጠገን ወደ ብልጽግና የምታደርገውን ጉዞ እያፋጠነች ትገኛለች፡፡እስካሁን የጀመረቻቸው ሪፎርሞች እየተሳኩ፤ የወጠነቻቸው ኢኒሼቲቮች ፍሬ እያፈሩ፤ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላት ተሰሚነት እየጨመረ፤ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስከበር የምታደርገው ጥረት ውጤት እያስመዘገበ መሆኑ ለዚህ ምስክር ነው፡፡ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና አጋሮች ጋር በተደረጉ ውይይቶች እየተገኙ ያሉ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ድጋፎች ለፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሪፎርሞች ስኬት ያላቸው አበርክቶ ከፍተኛ ነው፡፡
በልማትና በፖለቲካ መስክ እየመጡ ያሉ አዎንታዊ ለውጦች ሀገራዊ ሰላም እንዲጸና አስተዋጽዖ ያበረክታሉ፡፡ ሀገራዊ የሰላም ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ ይሄንንም የምክር ቤቱ ግምገማ አመላክቷል፡፡ ከኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጥ በተጨማሪ የሰላም ሁኔታው እንዲሻሻል ያደረጉ ምክያቶችም አሉ፡፡ ሕዝቡ የግጭትንና የጦርነትን አስከፊ ገጽታ በማየት ከግጭት ጠማቂዎች ጋር ላለመተባበር ያሳየው ቆራጥነት የመጀመሪያው ነው፡፡ መንግሥት ለሰላማዊ መፍትሔ ያለው የጸና አቋም እና ያደረገው እንቅስቃሴ በሁለተኛነት የሚጠቀስ ነው፡፡
ምንም እንኳን በአንዳንድ ወገኖች እኩይ ዓላማ የተነሣ የትግራይ ሕዝብ የሚፈልገውን ያህል ሰላም ባያገኝም፣ በትግራይ የነበረው ጦርነት በሰላም እንዲፈታ መንግሥት ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት ሕዝቡ እፎይታ እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡ የሰላም ስምምነቱ መንግሥታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥራዎች እንዲከናወኑ፣ መሠረተ ልማቶችም እንዲጠገኑ አድርጓል፡፡ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎችም መንግሥት ሕግ በማስከበርና የሰላም መንገዶችን በማበረታታት ባከናወነው ተግባር አያሌ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ ታጣቂዎች የሰላም መንገድን መርጠው በሰላም ገብተዋል፡፡ ሕዝብ የሰላም ባለቤት በመሆን አካባቢውን ማስከበር ጀምሯል፡፡ ክልላዊ የጸጥታ መዋቅሮች ተጠናክረዋል፡፡ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በታቀደላቸው መንገድ መከናወን ጀምረዋል፡፡ የሸቀጦችና የሰዎች ዝውውሮች የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ በሌሎችም የሀገራችን አካባቢዎች የሰላምና የጸጥታ ሁኔታው ይበልጥ እየጸና እንደሚገኝ የደኅነት ምክር ቤቱ በጥልቀት ገምግሟል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ካለበት ነባራዊ ሁኔታ፣ ዓለም እየሄደች ከምትገኝበት የፖለቲካና የኢኮኖሚ መንገድ፣ እንዲሁም ሀገራችንን ልናደርስ ከምንፈልግበት የብልጽግና ደረጃ አንጻር ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መኖራቸውንም ምክር ቤቱ ተመልክቷል፡፡
የመጀመሪያው በሃያ አንደኛው መክዘ ሊኖር የማይገባውን፣ ፍላጎትን በኃይል የማስፈጸም ኋላ ቀር አማራጭ የሚከተሉ አካላትን የተመለከተ ነው፡፡ እነዚህ አካላት መልካቸው ይለያይ እንጂ በተለያዩ አካባቢዎችና በውጭ ይገኛሉ፡፡ የራሳቸውን አካባቢ ከሌላው የበለጠና የተጎዳ አድርገው ያያሉ፡፡ መነጋገርና መወያየት አይፈልጉም፡፡ ሤራ፣ ወጥመድ፣ ዝርፊያ፣ እገታ፣ ጭካኔ፣ ሕገ ወጥ ንግድ እና ፍላጎት በኃይል ብቻ ማስፈጸም መለያቸው ነው፡፡ አልፎ አልፎም ጥፋት የጋራ ዓላማቸው በመሆኑ ተቀናጅተው ለማጥፋት ይሞክራሉ፡፡ ሕጋዊ የፓርቲ ሽፋኖችን ለሕገ ወጥ ተግባራት ይጠቀማሉ፤ ከኃላፊነት የተነሡ አኩራፊ ፖለቲከኞችን በመጠቀም ሕገ ወጥ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፤ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለሑከት ተግባር ለመጠቀም ይሠራሉ፡፡
ሁለተኛዎቹ አካላት በተለያዩ ቦታዎች ተቀምጠው፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በመተባበር፣ የመንግሥትን ሥራዎች በማደናቀፍ፣ የሕዝብን ምሬት በመጨመርና የሐሰት ወሬዎችን በማዛመት የተጠመዱ ናቸው፡፡ በማኅበራዊ ቦታዎች፣ በቤተ እምነቶች፣ በመሥሪያ ቤቶች እና በንግድ ቦታዎች ተሠግሥገው እኩይ ዓላማቸውን ለማስፈጸም ይሞክራሉ፡፡ ሸቀጥ ይደብቃሉ፤ የአቅርቦት እጥረት ይፈጥራሉ፤ የውጭ ምንዛሬ ሥርጭትን ይገድባሉ፤ ኮንትሮባንድ ያካሂዳሉ፤ በሕገ ወጥ መንገድ ሰዎችንና መሣሪያዎችን ያዘዋውራሉ፡፡ በሙስና፣ በዘመድ አዝማድ እና በብልሹ አሠራር ሕዝብ እንዲማረር ሆን ብለው ይሠራሉ፡፡
ሦስተኛዎቹ የሐሰት ፕሮፓጋንዳውን የሚመሩ ክንፎች ናቸው፡፡ መደበኛውንና ማኅበራዊውን ሚዲያ በመጠቀም የሕዝቡን ሰላም ይረብሻሉ፡፡ በጦር ሜዳ ሲሸነፉ፤ ሤራዎቻቸው ሲከሽፉባቸው፤ በሰልፍና በዐመጽ የሚወድቅ መንግሥት ሲያጡ፤ የመጨረሻ አማራጫቸውን በመጠቀም ላይ ይገኛሉ፡፡ የሐሰት ታሪክ ይፈጥራሉ፤ የሐሰት መረጃ ይቀምራሉ፤ የሽብር ወሬ ያደራሉ፤ የሑከት ዜና ይፈበርካሉ፡፡ የፖለቲካ፣ የአስተዳደርና የጸጥታ ተቋማት ከሕዝቡ ጋር ተቀናጅተው በሚሠሩት ሥራ የጥፋት ኃይሎች ዓላማ እንዳይሳካ፣ ዐቅማቸው፣ ምኞታቸውም ከንቱ ሆኖ እንዲቀር ለማድረግ ተችሏል፡፡
ከእነዚህ ሀገራዊ የጸጥታ ሁኔታዎች በተጨማሪ ዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ ሁኔታዎችም በደኅንነት ምክር ቤቱ በጥልቀት ታይተዋል፡፡ የዓለም የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ እየተከሠቱ ያሉ ውጥረቶች፣ የሽብር እንቅስቃሴዎች፣ እየታወኩ ያሉ ዓለም አቀፍ የንግድ መሥመሮች፣ እየፈረሱ እና እየተዳከሙ የሚገኙ ሀገሮች፣ እየተበራከቱ ያሉ የሳይበር ጥቃቶች ፣ እየተነጣጠሉ ያሉ ነባር ዓለም አቀፋዊ ትብብሮች፣ እየተፈጠሩ ያሉ አዳዲስ ዓለም አቀፋዊ ጥምረቶች፤ በሀገራችን ላይ ሊያሳድሩት የሚችሉት ተጽዕኖ በዝርዝር ውይይት ተደርጎበታል፡፡
የተቀመጡ አቅጣጫዎች
ሰላም፣ ጸጥታና ደኅንነት ከፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሁኔታዎች ጋር የተሣሠሩ ናቸው፡፡ ፖለቲካዊ ብስለት፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና ማኅበራዊ መረጋጋት፣ የአንድን ሀገር የሰላም፣ የጸጥታና የደኅንነት ሁኔታዎችን ያሻሽላሉ፡፡ ከዚህ አንጻር በሀገራችን የተጀመሩ ሪፎርሞችን ወደ ማጽናት ምእራፍ ማድረስ ይገባናል፡፡ አምራችነትን ማበረታታት፣ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምን በተያዘለት ጊዜና ደረጃ መተግበር፣ ለወጣቶች ሥራ መፍጠርና ማሠማራት፣ የሰዎችንና የሸቀጦችን ዝውውር ይበልጥ ማቀላጠፍና ሰላማዊ ማድረግ፤ ኮንትሮባንድንና ሕገ ወጥ ንግድን መቆጣጠር፤ የመሠረተ ልማትን ደኅንነት በሕዝብና በጸጥታ አካላት ማረጋገጥ፤ የተጀመሩ ኢኒሼቲቮችን በመፍጠርና መፍጠን ስልት ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ፤ የበልግና የክረምት ሥራዎችን በተገቢ ዕቅድና አመራር ለውጤት ማብቃት፤ የትምህርት እና የጤና አገልግሎቶች በየትኛውም አካባቢ ፈጽሞ እንዳይቋረጡና የተቋረጡትም እንዲቀጥሉ ማስቻል አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት ተናብበው፣ ተቀናጅተውና በጋራ ዐቅደው የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጡ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በፖለቲካዊ ውይይት ለመፍታት የተጀመረው እንቅስቃሴ ፍሬ እያፈራ ነው፡፡ ይሄን ሥራ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ባህላዊ መንገዶችን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት ሰላማዊ መንገዶች መጠቀም ይገባል፡፡ የሰላም መንገድን መርጠው ለሚመጡ አካላት ተገቢውን ክብካቤ ማድረግ እና ሠልጥነው ወደ ሕዝቡ እንዲቀላቀሉ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሰላም አማራጮችን ዘግተው ፍላጎታቸውን በኃይል ለማስፈጸም በሚንቀሳቀሱት ላይ የተጀመረውን ሕግ የማስከበር ተግባር አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡
ከኢትዮጵያ ጠላቶች ተልዕኮ እየተቀበሉ በሀገር ውስጥ ችግር ለመፍጠር የሚጥሩ ባንዳ ኃይሎች ከዕለት ወደ ዕለት ዐቅማቸው እየደከመ፣ ተቀባይነታቸውም እየከሰመ መጥቷል፡፡ የገንዘብና የሰው ኃይል ምንጫቸውም እየነጠፈ ነው፡፡ ነገር ግን ፈጽመው እስኪጠፉ ድረስ ሕግ የማስከበር፣ የሰላም አማራጮችን አሟጦ የመጠቀም እና ሕዝብን የማንቃት ሥራዎች ወሳኝ ናቸው፡፡ ይሄን ካለፈው በበለጠ ለማከናወን የሚያስችል ስልትና አቅጣጫም በደኅንነት ምክር ቤቱ ተቀምጧል፡፡ ለዚህም የሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል አመራሮች በዕቅድ የተቀመጠውን ፈጥነው በመተግበር ውጤት ማምጣት እንዲቻል አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
በተለዩ መዋቅሮች ተደብቀው ሽብር የሚነዙ፣ የመንግሥትን ሥራ የሚያስተጓጉሉና ሕዝብን የሚያማርሩ፤ የተለያዩ ሚዲያዎችን በመጠቀም የሐሰት መረጃ የሚያሠራጩ አካላትን በመረጃና በማስረጃ ላይ ተመሥርቶ ለማጥራት የተከናወነውን ተግባር ምክር ቤቱ በአድናቆት ተቀብሎታል፡፡ አሁንም ቢሆን ግን እነዚህን አካላት ለማወቅ፣ ለሕግ ለማቅረብና ለማጥራት የሚያስችል ሥራ ይፈልጋል፡፡ ለዚህም በሕግ፣ በጸጥታ እና በሌሎች አካላት የሚከናወነው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡
ከሚመለከታቸው የሀገር ውስጥ እና የውጭ አካላት ጋር በመነጋገር እነዚህን የወሬ ጌቶች ለሕግ ለማቅረብ የተጀመሩ ሥራዎች ይበልጥ መቀጠል አለባቸው፡፡ ሐሰተኛ መረጃዎቻቸውን ሕዝብ እንዲያውቅ የማድረጉ ተግባር ዐቅምና ስልት ጨምሮ መከናወን አለበት፡፡ ከዚህም ባሻገር አግባብነት ባላቸው የሀገራችን ሕጎች አማካኝነት ተገቢውን ሕግ የማስከበር ሥራን ለመሥራት የሚመለከታቸው ሁሉ ዐቅደውና ተቀናጅተው እንዲሠሩ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
የተደራጁ የኢኮኖሚ ወንጀሎችንና አሻጥሮችን ማምከን፤ ብሎም ፈጻሚዎቻቸውን ለሕግ ማቅረብ ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር ነው፡፡ ከየትም አቅጣጫ የሚነሡ ሕገ ወጥ የሰዎች፣ የሸቀጦች እና የመሣሪያዎች ዝውውሮችን የሚከላከሉና የሚያስተካክሉ ሕጋዊና ተቋማዊ አሠራሮችን መዝርጋት ተገቢ ነው፡፡ የገንዘብ፣ የኢኮኖሚና የአስተዳደር ተቋማት ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን አስተዳደራዊና ሕጋዊ ርምጃዎች እንዲወስዱ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
የኢትዮጵያን ዓለም አቀፋዊ ተሰሚነት የሚያሳድጉ የዲፕሎማሲ ውጤቶች እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ ይሄን ይበልጥ በማስፋፋትና በማጠናከር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስከበር ተገቢ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት መብት ለማስከበር ዲፕሎማሲያዊ፣ ሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገዶችን መሠረት አድርጎ የተጀመረው ሥራ በተጀመረው ግለት እንዲቀጥል የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ያለው ሁኔታ እንዲረጋጋ፣ ለሕዝቦች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ትሥሥር እና ዕድገት ምቹ እንዲሆን፤ ውጥረቶች እንዲረግቡና ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ኢትዮጵያ የያዘችው አቋም ለዘላቂ ሰላምና ዕድገት ቁልፍ መሆኑን ተመልክተናል፡፡ በመሆኑም በቀጣናው ላይ ተገቢ የሆነውን ሚና ለመጫወት የሚያስችለን አቅጣጫ በምክር ቤቱ ተቀምጧል፡፡
ኢትዮጵያ በአሁናዊው የዓለም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ውስጥ የፖሊሲ ነጻነቷን አስጠብቃ፣ ጥቅሞቿን አስከብራ፣ ተገቢ ሚናዋን እንድትጫወት የተሰጠው ጥበብ የተሞላው አመራር የሚደነቅ ነው፡፡ ይሄው ጥበባዊ አመራር አሁንም ተጠናክሮ፣ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎችን ሁሉ ተሻግራ ተገቢ ሉላዊ ደረጃዋን እንድትይዝ ያደርጋል የሚል ጽኑ እምነት አለን፡፡ ሕዝባችንም ሰላሙን በመጠበቅና በማስከበር የጀመረውን አኩሪ ተግባር እንዲያጠናክር በዚሁ አጋጣሚ አደራ እንላለን፡፡ ወደ ሰላማዊ መንገድ የሚመጡ ታጣቂዎች ከዕለት ወደ ዕለት ቁጥራቸው እየጨመረ ነው፡፡ እነዚህን ታጣቂዎች ተቀብሎ ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ምትክ የሌለው ነው፡፡ በመሆኑም ለዚህ ሥራ የተቋቋሙ አካላት ከማኅበረሰቡ ጋር ይበልጥ ተቀናጅተው እንዲሠሩ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
በኃይል እና በዐመጽ ፍላጎትን የማስፈጸም መንገድ ከሽፏል፡፡ ውጤት እንደማያመጣም በተግባር ታይቷል፡፡ ይሄንን መንገድ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የተቀላቀሉ ወገኖች ወደ ሰላማዊ የሐሳብ መድረክ እንዲመጡ ጥሪ እናደርጋለን፡፡ መንግሥት ለሰላማዊ ውይይት ዛሬም ዝግጁ መሆኑን ደግመን እናረጋግጣለን፡፡
የጸጥታና የደኅንነት ተቋማት የሀገርን ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ እየከፈሉት ያለውን መሥዋዕትነት ምክር ቤቱ አድንቋል፡፡ የሀገራችን ሁለንተናዊ ብልጽግና እስኪረጋገጥ ድረስ የጀመራችሁትን የዐርበኝነት ተግባር እንድታጠናክሩ ደግመን አደራ እንላለን፡፡
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን የሰላምና የልማት ሥራዎች በመደገፍ እና እያስመዘገበች ላለችው ለውጥ ዕውቅና በመስጠት ላደረገው አስተዋጽዖ ምክር ቤቱ ያመሰግናል፡፡ ኢትዮጵያ በቀጣናው፣ በአህጉሩና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምንና ደኅንነትን ለማረጋገጥ የነበራትንና ያላትን ከፍተኛ ሚና በመረዳት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁለንተናዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል በዚሁ አጋጣሚ አደራ እንላለን፡፡
የሀገራችን ብልጽግና አይቀሬ ነው፡፡ ከጅምሩ የተገኙ ውጤቶችም ይሄንን ይመሰክራሉ፡፡ ሪፎርሞቻችንና ኢኒሼቲቮቻችን ፍሬ እያፈሩ ናቸው፡፡ ፈተናዎች እያለፉ፤ ቋጠሮዎች እየተፈቱ፤ ችግሮች እየተቀረፉ በመሄድ ላይ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሚና ይበልጥ እየተጠናከረ መጥቷል፡፡ የሰላም፣ የጸጥታና የደኅንነት ሥራዎቻችንን ይበልጥ አጠናክረን፣ ተቀናጅተንና ተናብበን በማከናወን የሕዝባችንን ርካታ ለማረጋገጥ ያለንን ዝግጁነት በዚሁ አጋጣሚ እናረጋግጣለን፡፡
የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት
ሚያዚያ 1፣ 2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ