Fana: At a Speed of Life!

ሚኒስቴሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተግባራዊ የማድረግ ሃላፊነቱን እየተወጣ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የገንዘብ ሚኒስቴር የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተግባራዊ የማድረግ ሃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ገለጹ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የገንዘብ ሚኒስቴርን የ8 ወራት የሥራ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡

አሕመድ ሺዴ በዚህ ወቅት ÷ የፊሲካል ፖሊሲውን በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ የዋጋ ንረትን በማረጋጋት እና ለመሰረታዊ ግብዓቶች ከ300 ቢሊየን ብር በላይ ድጎማ መደረጉን አንስተዋል፡፡

በዚህም አጠቃላይ የመንግስትን ፋይናንስ በአግባቡ በማስተዳደር የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ ፕሮግራም ውጤታማ በማድረግ ተቋሙ ሃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የፊሲካል ፖሊሲንና የመንግስት ፋይናንስን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ ባለፉት 8 ወራት ተቋሙ የኑሮ ወድነት የሚያድግበትን ፍጥነት ለመቀነስ በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የኦዲት ግኝቶች ላይ ተገቢውን ርምጃ ከመውሰድ አንጻር የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ነው የገለጹት፡፡

በቀጣዩ 2018 በጀት ዓመት የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ ፕሮግራሙ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የዋጋ ንረቱ የሚጨምርበት ፍጥነት ይበልጥ እንዲቀንስ ጥረት እንደሚደረግ መጠቆሙንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.