በጋምቤላ ክልል ምርታማነትን ለማሳደግ ባለድርሻዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጋምቤላ ክልል የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የዘርፉ ባለድርሻዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ ጥሪ አስተላለፉ።
በክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የግብርና ልማት አጋር አካላት ግንኙነት አማካሪ ካውንስል 1ኛ ዙር የምክክር መድረክ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድሯ በመድረኩ እንዳሉት፤ ክልሉ በዝናብም ሆነ በመስኖ ሊለማ የሚችል ለም መሬት አለው።
በቂ የከርሰ ምድር እና የገጸ-ምድር ውሃ ሃብት ቢኖርም የክልሉ ግብርና በዝናብ ላይ ብቻ የተመሰረተ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም በአየር ንብረት ለውጥ ምንክያት ጎርፍ፣ ድርቅ እና የዝናብ መቆራረጥና ስርጭት አለመስተካከል የመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች በአርሶ እና ከፊል አርብቶ አደሮች ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርሱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
በተጨማሪም ዘላቂነት ያለው የግብርና ልማት እንዲኖር እና ምርታማነት እንዲያድግ በዘርፉ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።