ኦብነግ የድርጅቱን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር አከናውነዋል ያላቸውን ሊቀመንበር ከኃላፊነት አነሣ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) የግንባሩን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር ያከናወኑትን ሊቀመንበር አብዲራህማን ማሃዲ ከኃላፊነት አነሣ።
የኦብነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው።
ግለሰቡ ከድርጅቱ ሊቀመንበርነት የተነሱበት ምክንያት የግንባሩን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግባራትን በማከናወናቸው እንደሆነ ተገልጿል።
ግንባሩ መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ ወደ ሀገር ከገባ ጊዜ አንሥቶ ሰላማዊ ትግል ለማካሄድ ለሕዝብ የገባው ቃል ተግባራዊ እንዳይሆንም ግለሰቡ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ተጠቁሟል።
ኦብነግ ነሐሴ 6 ቀን 2010 ዓ.ም መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ ሰላማዊ ትግል ለማካሄድ ወደ ሀገር መግባቱ ይታወሳል።
ማዕከላዊ ኮሚቴው እያካሄደ በሚገኘው መደበኛ ስብሰባ በቀጣይ ለሚካሄደው ጉባኤ የጉባዔ አደራጅ ኮሚቴ ይመርጣል ተብሎ ይጠበቃል።