በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው ባንክ ተከፈተ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሰመር ካምፕ እና በክኅሎት ኢትዮጵያ መርሐ-ግብር የተሠሩ የፈጠራ ውጤቶች የክኅሎት ባንክ ተከፍቷል።
ባንኩን የሥራና ክኅሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል መርቀው መክፈታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በክኅሎት ባንኩ የሚገኙት የፈጠራ ውጤቶች ባለፈው ዓመት የሰመር ካምፕ ፕሮግራም እንዲሁም በዘንድሮ የክኅሎት ኢትዮጵያ ተሳታፊዎች የተሠሩ እና እየተሠሩ ያሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ይህ በፌዴራል የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የሚገኘው የክኅሎት ባንክ፤ የቴክኖሎጂ ባለቤቶችን የፈጠራ ምርቶችን መጠቀምና ማስመረት ከሚፈልጉ ደንበኞች ጋር የሚያገናኝ መሆኑ ነው ተብሏል፡፡
ባንኩ ለጎብኚዎች ክፍት ሲሆን፤ የመንግሥት እና የግል ሴክተሮች የፈጠራ ውጤቶችን በመጎብኘት እንዲመረትላቸው የሚፈልጓቸውን ምርት ትዕዛዝ መስጠት የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ መኖሩም ተመላክቷል፡፡