Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መስመር የሚያጋጥም ችግር የብልጽግና ጉዞን ያስተጓጉላል- ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መስመር ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች ሀገራችን የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ያስተጓጉላሉ ሲሉ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ሚኒስትሩን ጨምሮ የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) በአፋር ክልል አዋሽ ሰባት ተገኝተው በኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መስመር ደኅንነት ዙሪያ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም፤ በተለይ በቅርብ ጊዜ በባቡሩ ኤሌክትሪክ መስመር ላይ ጉዳት እና ስርቆት መድረሱን ተከትሎ ችግሩን ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በውይይቱ ላይ እንደገለጹት፤ በባቡሩ መስመር ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታትና በሙሉ ዐቅም መጠቀም እንዲቻል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ሥራ ያስፈልጋል።

መስመሩ የኢትዮጵያ የወጪ እና ገቢ ዕቃዎች የሚጓጓዙበት መሆኑን አስገንዝበው፤ በአካባቢው የሚያጋጥሙ ችግሮች ሀገራችን የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ያስተጓጉላሉ ብለዋል፡፡

በተጨማሪም እንደ ሀገር በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ መሆን እንዳይቻል እና ዕቃዎችን በመንገድ ላይ በማዘግየት ለተጨማሪ ጊዜና ወጪ ያጋልጣሉ ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.