Fana: At a Speed of Life!

የግብርና መሠረታዊ ምርት 45 በመቶ ከእንስሳት ሀብት ዘርፍ እየመነጨ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ሀገራት ውስጥ እንደምትገኝ እና ዘርፉም ከአጠቃላይ ግብርና መስክ 45 በመቶ እያበረከተ መሆኑን የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የከተሞች መስፋፋት፣ የወተትና ወተት ተዋጽዖ ፍላጎት ማደግ ምርታማነትን ለማሳደግ በወሳኝነት የእንስሳት ዝርያ መሻሻል አስገዳጅ ሁኔታዎች መሆናቸውን በኢንስቲትዩቱ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዳኛቸው በየነ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በዳልጋ ከብት ምርምር ላይ በስፋት እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ በበግና ፍየል ላይም በማኅበረሰብ አቀፍ የዝርያ ማሻሻል ላይ በቅንጅት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃም አምስት የአባላዘር ማምረቻ ላብራቶሪዎች መቋቋማቸውን ለፋና ዲጂታል ገልፀዋል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ከ3 ሚሊየን በላይ የወተት ላሞች እና ጊደሮችን ማዳቀል መቻሉን ጠቅሰው፤ ይህን ተከትሎም ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ዝርያቸው የተሻሻሉ ጥጆች መወለዳቸውን ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ ከ11 ሺህ በላይ የተመረጡ በጎች እና ከ2 ሺህ 896 በላይ አውራ ፍየሎችን ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት መቻሉንም ገልጸዋል።

በሆለታ የእንስሳት ልማት ማዕከል እና በሌሎች ስድስት ማዕከላት የጊደር ማባዣ ማዕከላት ላይ ዝርያቸው የተሻሻሉ ጊደሮችን በማፍራት ለአርቢው ሕብረተሰብ እንዲተላለፉ በመደረግ ላይ እንዳለም ጠቅሰዋል፡፡

በዝርያቸው እና በምርታማነታቸው የተመረጡ ኮርማዎች ከተመዘገቡ የኢንስቲትዩቱ የእርባታ ጣቢያዎች መረጃ በመነሳት፤ ለአባለዘር ምርት ሊሆኑ የሚችሉት በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ተለይተው ወደ ኢንስቲትዩቱ እንደሚገቡም ተናግረዋል።

የተለዩትን ኮርማዎች በመንከባከብና በማሳደግ የአባላዘር ምርት በመሰብሰብ በከፍተኛ ጥንቃቄ በየዶዙ በማሸግና በፈሳሽ ናይትሮጅን ውስጥ ዘሩ በሕይዎት እንዲቆይና ለአርሶ/አርብቶ አደሩና በግልም ሆነ በኢንቨስትመንት በአዳቃይ ቴክኒሺያኖች አማካኝንት የማዳቀል አገልግሎት በመስጠት የዝርያ ማሻሻል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ1 ሚሊየን በላይ ዶዝ አባላዘር በማምረትና በማሰራጨት የሀገሪቱን የዝርያ ማሻሻል በሚፈለገው መልኩ ለማስኬድ እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.