ለቴሌግራም ተጠቃሚዎች የተላለፈ የጥንቃቄ መልዕክት❗️
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢንተርኔት አጠቃቀም በየቀኑ እየጨመረ በሄደበት በዚህ ዘመን፣ ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ስጋቶችም እየተስፋፉ ነው።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በቅርቡ በርካታ አደገኛ የኢንተርኔት አድራሻዎችን (URLs) መርምሮ፣ እነዚህ አድራሻዎች ለሀገራችን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች በይበልጥ የቴሌግራም ተጠቃሚዎች አካውንቶችን በመንጠቅ ከፍተኛ ስጋት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አረጋግጧል።
ከተለያዩ አካላት በቴሌግራም የሚደርሱ ሊንኮች በርካታ አደጋዎችን የሚይዙ ሲሆን፣ የሚከተሉት አደጋዎች በዋናነት ይገኙበታል፡፡
👉የግል መረጃ መጠለፍ:- እንደ የባንክ መለያ ወይም የይለፍ ቃል ያሉ መረጃዎችን መሰረቅ፤
👉የማልዌር ስርጭት:- ስልኮችን ወይም ኮምፒውተሮችን የሚጎዱ ቫይረሶች፤
👉ማጭበርበሪያ:- ተጠቃሚዎችን በሀሰተኛ ተስፋዎች (እንደ ውርርድ ወይም ኢንቨስትመንት) መታለል፤
በመሆኑም ማኅበረሰቡ በቴሌግራም አማካኝነት የሚላኩለትን አጠራጣሪ ሊንኮች ከመክፈት እንዲቆጠብ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ባወጣው መረጃ አሳስቧል።
ሰሞኑን በቴሌግራም ከሚላኩና በፍጹም መከፈት የሌለባቸውን ሊንኮች አስተዳደሩ በምስል አጋርቷል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቴሌግራም አጠራጣሪ የሆኑ ሊንኮች ካጋጠሙ ለኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በ e-mail ethiocert@insa.gov.et እና 933 ነጻ የስልክ መስመር ማሳወቅ እንደሚቻል አስታውቋል፡፡