ለጋምቤላ ከተማ ኮሪደር ልማት ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጋምቤላ ከተማ የኮሪደር ልማት የገቢ ማሰባሰቢያ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ በተገኙበት እየተካሄደ ነው።
የጋምቤላ ከተማ የኮሪደር ልማት የመጀመሪያው ምዕራፍ እየተከናወነ ሲሆን÷ በልማቱ ሕዝቡን ተሳታፊ ለማድረግ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር እንዳስፈለገ ተገልጿል።
ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ በዚህ ወቅት÷ የኮሪደር ልማቱ መሰራት የከተማዋን ገፅታ አጉልቶ የሚያወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
ልማቱን ለማከናወን በመንግስት በጀት ብቻ ማጠናቀቅ ስለማይቻል ሕዝቡ ድጋፍ በማድረግ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የክልሉ ሕዝቦች፣ በክልሉ በተለያዩ ሥራዎች የተሰማሩ ባለሀብቶች፣ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሀገር በቀልና ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች፣ የጋምቤላ ክልል ተወላጆችና የጋምቤላ ከተማን ኮሪደር ልማት ለመደገፍ ፍቃደኛ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ ማቅረባቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።