ኮሚሽኑ አሳታፊና አካታች የሀሳብ ውክልና እንዲኖር እየሰራ ነው ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አሳታፊና አካታች የሀሳብ ውክልና እንዲኖር እየሰራ መሆኑን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም ገለጹ።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአማራ ክልል ባለድርሻ አካላትን ያካተተው የምክክር መድረክ ተጀምሯል።
የወረዳ ማኅበረሰብ ተወካዮች የአጀንዳ ማሠባሠብና ለአጠቃላይ የምክክር ጉባዔው ወኪሎችን የመምረጥ ሥራ ሚያዝያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም መጠናቀቁ ይታወሳል።
ከዛሬ ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም በሚካሄደው የምክክር ሒደት የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ማኅበራት ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና በመጀመሪያው ዙር ምክክር ለሀገራዊ የምክክር ጉባዔ የተመረጡ የወረዳ ማኅበረሰብ ወኪሎች ተሳትፈዋል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፤ ኮሚሽኑ ላለፉት አምስት ቀናት በክልሉ ያካሄደው የማህበረሰብ ወኪሎች አጀንዳ ልየታ ስራ ከፍተኛ ክንውን የተመዘገበበት ነበር ብለዋል።
ኮሚሽኑ አሳታፊና አካታች የሀሳብ ውክልና እንዲኖር እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ሒደቱ ሁሉንም የሚያስተናግድ እንደሆነ አረጋግጠዋል።
የዚህ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ተሳታፊዎች አጀንዳ የመለየትና የማጠናቀር እንዲሁም ለጠቅላላ ጉባኤው የሚሳተፉ ተወካዮች የሚመረጡበት እንደሆነ አመልክተዋል።
መላው የአማራ ህዝብ የአማራ ክልል ጉዳይ ይመለከተዋል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የታጠቁ ቡድኖች እና በውጭ ያሉትን ጨምሮ ሁሉም የአማራ ክልል ተወላጆች ሀሳባቸውን የሚሰጡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ኮሚሽኑ ቁርጠኛ ነው ብለዋል።
በመሳፍንት እያዩ