Fana: At a Speed of Life!

ፋና የስልጠና ማዕከል አገልግሎት መስጠት ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሥልጠና ማዕከል ዕውቅና ባገኘባቸው አራት የሙያ መስኮች መደበኛ ስልጠና መስጠት መጀመሩን ዛሬ አብስሯል።

ማዕከሉ ከዚህ ቀደም በጋዜጠኝነት፣ በሚዲያ ኮሙኒኬሽን እና በሚዲያ ቴክኖሎጂ የስልጠናና የማማከር ስራ ሲሰራ ቆይቷል።

ዛሬ በተካሄደው የማስጀመሪያ መርሐ ግብር ማዕከሉ በብሮድካስት ጆርናሊዝም፣ በብሮድካስት ቴክኖሎጂ፣ ግራፊክስ እና ቪዲዮ ግራፊና ፎቶግራፊ የሙያ መስኮች በሰርተፊኬት ደረጃ መደበኛ ስልጠና መስጠት ጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት÷ ተቋሙ በሚዲያ ዘርፍ የካበተ ልምድ ያለው በመሆኑ የሥልጠና ማዕከሉን ዕውን ማድረግ እንዳስፈለገ ተናግረዋል።

ፋና በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን እና በዲጂታል ሚዲያ ያለውን የዳበረ የሙያ ክህሎት ማዕከል ከፍቶ በመደበኛነት ዕውቀት ማጋራት ይገባዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ለማዕከሉ ዕውቅና የሰጡ አካላት ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከዚህ ቀደም ካበረከታቸው አስተዋጽዖዎቹ በተጨማሪ ነገ የተሻለ እንደሚሰራ በማመን እንደሆነ መግለጻቸውን ጠቅሰዋል።

ማዕከሉ ለውስጥ ሰራተኞች ስልጠና የሚሰጥ፣ መደበኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ በሚዲያ ዘርፍ ብቁ የሚያደርግና ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣትም ዕውቀቱን ለማጋራት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ዘመኑ የዲጂታል በመሆኑ በዘርፉ ያለውን ትልቅ አቅም በስልጠና እንደሚያገራ ተናግረዋል።

የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው በበኩላቸው÷ ማዕከሉ ዕውን እንዲሆን ድጋፍና ትብብር ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበው፤ በሚዲያ ዘርፍ የልህቀት ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግል አረጋግጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.