Fana: At a Speed of Life!

የአሜሪካና ሩሲያ የሁለትዮሽ ውይይት በኢስታንቡል መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሁለተኛው ዙር የአሜሪካ እና ሩሲያ ውይይት በቱርክ ኢስታንቡል መካሄድ ጀምሯል፡፡

በአሜሪካ የሩሲያ አምባሳደር አሌክሳንደር ዳርኪቭ እና በአሜሪከ ረዳት ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሶናታ ኮልተር አማካኝነት የተመሩት የሁለቱ ሀገራት ልዑካን ቡድኖች የሀገራቱን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ተመላክቷል፡፡

በኢስታንቡል በሚገኘው የሩሲያ ቆንስላ ውስጥ እየተካሄደ የሚገኘው ውይይት በዋናነት በአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ዘመን የሻከረውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማስተካከል ያለመ ስለመሆኑም ነው የተገለፀው፡፡

የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ የተወረሱ የሩሲያ ንብረቶችን እና የባንካ ሂሳቦች መመለስ እና ከሞስኮ ወደ ዋሽንግተን ቀጥታ በረራ መጀመር የምክክሩ ቀዳሚ አጀንዳዎች እንደሚሆኑም ተጠቁሟል።

የአሜሪካ እና ሩሲያ ልዑክ የመጀመሪያ ዙር ውይይት በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ በኢስታንቡል የአሜሪካ ኤምባሲ ውስጥ መካሄዱን ቲ አር ቲ ወርልድ እና ስፑትኒክ በዘገባቸው አስታውሰዋል።

በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ገለልተኛ አቋም ያላት እና ከሁለቱ ሀገራት ጋር ጠንካራ ግንኙነት ያላት ቱርክ ሩሲያ እና አሜሪካ ወደ ቀድሞ ወዳጅነታቸው እንዲመለሱ የአዳራደሪነት ሚናዋን እየተወጣች መሆኑም ተነግሯል።

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.