ፓኪስታን ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው የኢኮኖሚ ዕድገት ለሌሎች አርአያ መሆን እንደሚችል ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ከፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር የውጭ ግንኙነት ልዩ አማካሪ ሰይድ ታሪቅ ፋጢሚ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በሀገራቱ ሰላም፣ ብልጽግና እና የዘላቂ ልማት የጋራ ግቦችን ለማሳካት የባለብዙ ወገን ትብብርን ጨምሮ በጋራ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ አቪዬሽን፣ ቴክኖሎጂና አየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አምባሳደር ጀማል (ዶ/ር) ÷ፓኪስታን በፈረንጆቹ በ2025 በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ም/ቤት ተለዋጭ አባል ሆና በመመረጧ ለፓኪስታን ሕዝብና መንግስት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) የ“መደመር” ፍልስፍና መሰረት ያደረጉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ የውጭ ግንኙነትና የሕግ ማሻሻያዎች ዙሪያም ገለጻ አድርገዋል፡፡
ለውጡን ተከትሎ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች ከሚዘጋጁባቸው ግንባር ቀደም ሀገራት ተርታ መሰለፍ መቻሏን ጠቅሰዋል።
ሰይድ ታሪቅ ፋጢሚ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ መንግስት በክልላዊ እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ እየተጫወተ ላለው ሚና አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው አስደናቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ለሌሎች ሀገራት አርአያ መሆን እንደሚችል አስገንዝበዋል፡፡
በቀጣይም በሁለቱ ሀገራት መካከል የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ትብብርን በይበልጥ ለማሳደግ ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ማረጋገጣቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡